በዘመናችን ያለው የአብዛኛው ስብከት ችግር እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ-መለኮት እንደ መፍትሔ

ምርመራ፦ በዘመናችን ያለው የአብዛኛው ስብከት ችግር (ክፍል 1)

እኔ አባል በሆንኩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ውስጥ (የደቡብ ባፕቲስት ኮንቬንሽን)፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ስሕተት አልባ መሆናቸውን ለማሳየት የተደረገው ጦርነት ድል ተደርጎ ሊሆን ይችላል። ሆኖም፣ እኛ ሆንን ሌሎች የወንጌላውያን ቤተ እምነቶች ወይም ተመሳሳይ ጦርነቶችን ያሸነፍን አብያተ ክርስቲያናት፣ ራሳችንን ቶሎ ማመስገን የለብንም። ወግ አጥባቂ አብያተ ክርስቲያናት የቅዱሳት መጻሕፍትን ስሕተት አልባነት ሊቀበሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በቂ መሆኑን በተግባር ይክዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የማይሳሳት የእግዚአብሔር ቃል ነው ልንል እንችላለን፤ ሆኖም ግን በቁም ነገር በመድረኮቻችን ማወጅ ተስኖናል።

ዛሬ በብዙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የእግዚአብሔር ቃል ራብ አለ። አብዛኛውን ጊዜ ስብከቶች የሚያተኩሩት፣ የተሳካ ትዳር ለመመሥረት ወይም በባሕላችን ልጆችን ማሳደግ የሚቻልበት መንገድ ላይ ነው። በርግጥ በቤተ ሰብ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ስብከቶች ተስማሚ እና አስፈላጊ ናቸው። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሁለት ችግሮች ይከሰታሉ። በመጀመሪያ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚናገሩት ነገር በአብዛኛው ችላ ይባላል። ምን ያኽሎቹ ስብከቶች ጳውሎስ ስለ ወንዶች እና ሴቶች ሚና ምን እንደሚል በታማኝነት እና በአስፈላጊ ጊዜ ይናገራሉ (ኤፌሶን 5፥22-33)? ወይስ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚናገሩት እናፍራለን?

ሁለተኛ፣ እና ምናልባትም ከዚህ በከፋ ሁኔታ እንደዚህ ዐይነት ስብከቶች የሚሰበኩት (ሁልጊዜም ማለት ይቻላል) በጎንዮሻዊ ደረጃ (horizontal level) ነው። ምእመኑ በየሳምንቱ እንዲመላለስ ብቻ የሚያደርጉ ማጣበቅያ ስብከቶች ናቸው፤ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚንጸባረቀው እና ለሕይወት ሁሉ መሠረት የሆነው ነገረ መለኮታዊ እይታ በቸልታ ታልፏል። መጋቢዎቻችን ከሳምንት እስከ ሳምንት ደስተኛ ሕይወት እንዴት መኖር እንዳለብን ምክር እየሰጡ፣ የሥነ ምግባር አስተማሪዎች ሆነው ይታያሉ።

ብዙ ጉባኤዎች ምን እየተከናወነ እንዳለ በወጉ አይረዱትም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ስብከት የሚያስተምረው ሥነ ምግባራዊ ሕይወት፣ ቢያንስ በከፊልም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ጋር ይስማማል። ይህም አማኞችም የማያምኑትም ያስፈልገናል ብለው ለሚያስቡት ነገር የሚቀርብ ስብከት እንዲሆን ያደርገዋል።

መጋቢዎች ስብከታቸውን በተረት እና በምሳሌዎች መሙላት እንዳለባቸው ያምናሉ፤ ስለዚህም ተረቶቹ የተገለጸውን የሞራል ነጥብ ይገልጻሉ። የትኛውም ጥሩ ሰባኪ ምሳሌዎችን ይጠቀማል። ነገር ግን ስብከቶች ምንም ዐይነት ነገረ መለኮትዊ አንድምታ በሌላቸው ታሪኮች ሊሞሉ ይችላሉ።

ወንጌላውያን አማኞች ደጋግመው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በነገረ መለኮት ትምህርት ጥሩ ሥራ እየሠሩ ነው፤ ምክንያቱም ጉባኤው ስለምናስተምረው ነገር ቅሬታ የላቸውም ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንዲህ ዐይነቱ አስተያየት በጣም አስፈሪ ነው። እኛ መጋቢዎች “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” የማወጅ ኀላፊነት አለብን (የሐዋርያት ሥራ 20፥27)። ጥሪያችንን እየፈጸምን መሆን አለመሆናችንን ለማወቅ፣ በጉባኤ ምርጫዎች ላይ መተማመን አንችልም። ቅዱሳት መጻሕፍት በሚጠይቁት ላይ መመሥረት አለብን። አንድ ጉባኤ የእግዚአብሔርን ቃል በሥርዐት ተምሮ የማያውቅ ሊሆን ስለሚችል፣ እኛ እንደ መጋቢዎች የደከምንበትን ቦታ እነርሱ ላይረዱት ይችላል።

ጳውሎስ፣ “ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሠርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ” ሲል አስጠንቅቆናል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ፣ “ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ“ በማለት ተናግሯል(2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥3-4)። ስብከታችንን የምንገመግመው ቅዱሳን በሚፈልጉት መሠረት ከሆነ፣ ለስሕተት ትምህርት በር እያዘጋጀን ይሆናል። ምእመኖቻችን መናፍቃን ናቸው እያልኩ አይደለም፤ ይልቁኑ ከሕዝብ አስተያየት ይልቅ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ የታማኝነት መለኪያ መሆን አለበት። የመጋቢዎች ጥሪ መንጋውን በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግቡ እንጂ፣ ሰዎች መስማት የሚፈልጉትን በማቅረብ ደስ እንዲሰኙ መጣር አይደለም።

ብዙውን ጊዜ ጉባኤዎቻችን፣ በሰባኪዎቻችን ጥሩ ሥልጠና አልተሰጣቸውም። የሥነ ምግባር ስብከት ጉባኤን ሁሌ ስንመገብ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡ? ደግ፣ ይቅር ባይ፣ አፍቃሪ እና ጥሩ ባል ወይም ሚስት መሆንን ይማሩ ይሆናል (በርግጥ ሁሉም መልካም ነገሮች ናቸው!)። ልባቸው ሊሞቅ አልፎ ተርፎም ሊታነጽ ይችላል። ነገር ግን የነገረ መለኮት መሠረቱን ችላ እስከ ተባለ ድረስ፣ የስሕተት ተኩላ ይበልጥ በቅርበት በጉባኤው ይሸሸጋል። እንዴት? መጋቢው ራሱ ስሑት ስለ ሆነ አይደለም። እርሱ በራሱ ነገረ መለኮት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እና ታማኝ ሊሆን ይችላል። እርሱ ግን በስብከቱ ሁሉ፣ ነገረ መለኮትን በውስጥ አዋቂነት ስለሚያስበው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትርክትና ነገረ መለኮት ለሕዝቡ መስበክን ይዘነጋል።

ስለዚህ በሚቀጥሉት ወይም ሁለት ቀጣይ ትውልዶች ምእመናኑ ሳያውቁት የበለጠ ለዘብተኛ የሆነ መጋቢ ሊሾሙ ይችላሉ። ይህ አዲስ መጋቢ ደግሞ ሰዎች ጥሩ፣ ደግ እና የፍቅር ሰው መሆን እንዳለባቸው ይሰብካል። ጥሩ ትዳር እና የተለዋዋጭ ግንኙነቶችን አስፈላጊነት ያጎላል። ነገረ መለኮቱ ከእርሱ በፊት ከነበረው ወግ አጥባቂ መጋቢ ነገረ መለኮት ስለሚመሳስል፣ በኋላው ያሉ ሰዎች ልዩነቱን እንኳ ላያውቁ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ወግ አጥባቂው መጋቢ ነገረ መለኮትን አልሰበከም። ወግ አጥባቂው መጋቢ በቅዱሳት መጻሕፍት አለመሳሳት ያምን ነበር፤ በመጽሐፍ ቅዱስ በቂነት ግን አይደለም፣ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩትን ሁሉ ለጉባኤው አልሰበከም።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮትን ቸል ማለት ተንሰራፍቷል። ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች (አንዱ ስሙን ማስታወስ የማልችለው ግለሰብ፣ በአንድ ትልቅ ስታዲየም ውስጥ) ሰዎችን ወደ ፊት እንዲመጡ የጋበዘባቸው ገጠመኞች በአእምሮዬ ውስጥ አሉ። በስታዲየሙ የተዘጋጀው ፕሮግራም ለወንጌል ስብከት እንዲሆን ታስቦ ነበር፤ እውነት ለመናገር ግን ወንጌል አልተሰበከም ነበር። ስለተሰቀለው እና ስለተነሣው፣ ወይም ለምን እንደ ተሰቀለ እና እንደ ተነሣ ምንም አልተነገረም። እምነት ከሥራ ይልቅ ለምን እንደሚያድን ምንም አልተነገረም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ፊት መጡ፤ ደግሞም ምንም ጥርጥር የለውም የዳኑ ተብለው ተመዝግበዋል። እኔ ግን ጭንቅላቴን እየነቀነቅኩ ምን እየሆነ እንዳለ አሰብኩ። ቢያንስ አንዳንዶች በእውነት እንዲለወጡ ጸለይኩ፤ ማለትም ምናልባት የወንጌልን ይዘት በሌሎች አጋጣሚዎች በመስማት ቀድመው ያውቁ ይሆናል ብዬ በማሰብ ነው። በጎበኘሁት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ሁኔታው ​​ተመሳሳይ ነበር። ሰባኪው፣ “ወደ ፊት ኑ” እና “ዳኑ” የሚል አበረታች ግብዣ ቢያቀርብም ስለ ወንጌል ምንም ማብራሪያ አልሰጠም!

እንዲህ ያለው ስብከት፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ባልተለወጡ ሰዎች ሊሞላ ይችላል፤ የእነርሱም አደጋ እጥፍ ድርብ ነው፤ ምክንያቱም እንደ ተለወጡ እና መዳናቸውን ፈጽሞ ሊያጡ እንደማይችሉ መጋቢዎች አስረግጠውላቸዋል፤ ነገር ግን ከጅምሩ አልዳኑም። ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ እነዚሁ ሰዎች “መልካሙ ሁኑ” የሚለውን የድኅረ ዘመናዊ ዓለም አዲሱ ወንጌልን ከሳምንት እስከ ሳምንት ይመከራሉ።

ቶማስ ሽራይነር