መጋቢዎች ለሕዝባቸው እንዲጸልዩ የቀረበ ጥሪ

መጋቢ ለመሆን በእግዚአብሔር ከተጠራህ፣ ለሕዝብህ መጸለይ እንደምትፈልግ እርግጠኛ ነኝ። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ፍላጎት ብቻ በጭራሽ በቂ አይደለም።

ጌታችን የራሱን ሰዎች ደቀ መዛሙርቱን፣ “በዚህ ተቀመጡ ከእኔም ጋር ትጉ” ብሎ በጠየቀ ጊዜ ከሚወዱት ሰው ጋር በታማኝነት ለመትጋት እና ለመጸለይ ፍላጎት እንደ ነበራቸው እርግጠኛ ነኝ። እንዳለመታደል ሆኖ፣ ያ ፍላጎት ብቻ በቂ አልነበረም። ይልቁንም፣ እያንዳንዱ መጋቢ ወደ ጸሎት ሲመጣ “መንፈስ ዝግጁ ነው ሥጋ ግን ደካማ ነው” ለሚለው እውነት የማይረሱ ምሳሌዎች ሆነዋል (ማቴዎስ 26፥41)። እንቅልፍ አጥተህ ለሕዝብህ ለመጸለይ ምን ያህል ጊዜ አዲስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ግን ልክ “ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበር” እንደሚል ምን ያህሉን ጊዜ በዐይኖችህ መድከም የተነሣ ዕቅድህ ሳይሳካ ቀርቷል (ማቴዎስ 26፥43)?

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ጸሎትን በሚያበረታቱ የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች፣ የዛሉትን ዐይኖቻችንን ማበርታት ነው። እነዚህ ማሰላሰሎች ነፍሳችሁ “እኛ ግን በጸሎት… እንተጋለን” በሚለው ሐዋርያዊ ጩኸት እንድትነሣ ያደርጋታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ (የሐዋርያት ሥራ 6፥4)።

ለዚህም፣ ከጸሎት አልባ እንቅልፋችን ያስወጡናል ብዬ ተስፋ የማደርጋቸውን ስድስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን አቀርባለሁ።

  1. ለሕዝብህ አለመጸለይ ኀጢአት ነው

ጸሎት አልባነት ኀጢአት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ታማኝ መሆን አለብን። ስለ ሕዝቡ መጸለይ ያልቻለ መጋቢ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ ፈቃደኛ እንዳልሆነ መጋቢ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ክርስቲያን ከመሆናችን በጣም ጣፋጭ እውነታዎች አንዱ “የጽድቅ ባሪያዎች” መሆናችን ነው (ሮሜ 6፥18)። ምንም እንኳ “የሥጋ ምኞት” ወደ ኀጢአት የሚጎትተን ቢሆንም (ገላትያ 5፥16) አማኞች አሁንም ትክክል የሆነውን ለማድረግ የማያቋርጥ ፍላጎት አላቸው። እግዚአብሔር ሕጉን በአእምሯችንና በልባችን ጽፏል (ኤርምያስ 31፥33ዕብራዊያን 8፥10)፤ ስለዚህ ጽድቅን መውደድና ክፋትን መጥላት እንፈልጋለን (መዝሙር 45፥7ዕብራዊያን 1፥9)። መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ኀጢአትን እንዲታገሡ በፍጹም አይፈቅድም። መጋቢዎች ጸሎት አልባነትን በሕይወታቸው ውስጥ በመታገሥ ደስተኞች ሊሆኑ አይችሉም፤ ምክንያቱም ጸሎት አልባ መሆን ኀጢአት ነው።

ነቢዩ ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንደሚጸልይ ቃል በገባ ጊዜ በግልጽ፣ “እኔ ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት እግዚአብሔርን መበድል ከእኔ ይራቅ” (1ኛ ሳሙኤል 12፥23) በማለት ለእስራኤል ሕዝብ ተናግሯል። ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ሕዝቦች አለመጸለይ በአምላክ ላይ የተፈጸመ ኀጢአት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ሳሙኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል መሪ ነበር። ሳሙኤል እነዚህን የሕዝቡን ፍላጎቶች ብቻውን ሊያሟላ በሚችለው በጅሆቫ-ጃይራ ፊት ሳያቀርብ፣ ሕዝቡን እንደሚንከባከባቸው እንዴት ሊናገር ይችላል?  ሳሙኤል ሕዝቡ እግዚአብሔርን በጸሎት እንዲፈልጉ ካልመራቸው እንዴት የእግዚአብሔርን ሕዝብ እየመራሁ ነው ማለት ይችላል? የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሳይጸልይ መምራት ማለት  ያለ እንክብካቤ፣ ያለ አቅርቦትና ያለ ምሪት ሕዝቡን “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” መተው ማለት ነው (ማቴዎስ 9፥36)።  እንደ መጋቢዎች፣ ከኀጢአት እንድንሸሽ እና ጽድቅን እንድንከተል ተጠርተናል። ካለመጸለይ ኀጢአት መሸሽ ደግሞም ስለ ሕዝባችን የመጸለይን ጽድቅ እና አስደናቂ ልማድ መልበስን መማር አለብን።

2. ስለ ሕዝብህ መጸለይ እግዚአብሔርን ያከብራል

ስለ ጸሎት ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ መዝሙር 50፥15 ነው፤“በመከራ ቀንም ጥራኝ፤ አድንሃለሁ አንተም ታከብረኛለህ።”

እያንዳንዱ የጭንቅ ቀን እግዚአብሔርን የማክበር ዕድል ነው። የታመሙትን በማጽናናት፣ አዲስ የዳኑ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት በማድረግ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉትን በመምከር ስናሳልፍ አንዳንድ ጊዜ ከእውነተኛው ጥሪያችን የተዘናጋን መስሎ ሊሰማን ይችላል፣ ነገር ግን ይህ ስሕተት ነው።

በመንገዳችን የሚመጣ እያንዳንዱ ችግር እግዚአብሔርን ለእርዳታ በመጥራት እርሱን የማክበር አጋጣሚ ነው። ጸሎታችንን ሲመልስ እና በምንጸልይላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ሲሠራ ክብሩን ይወስዳል። የታመሙትን ሲያጽናና ወይም ያጋጠሙንን የሎጂስቲክስ ጉዳዮች ሲያስተካክል ሥራውን ስለ ሠራ ክብሩን እግዚአብሔር ይወስዳል።

ከመዝሙሮቹ በአንዱ ውስጥ ያለውን የጆን ኒውተን (1725-1807) ምክር መውሰድ እንችላለን፦

ነፍሴ ነይ! ልብስሽን አዘጋጂ፤

ኢየሱስ ጸሎትን መመለስ ይወዳል፤

እርሱ ራሱ እንድትጸልዪ አዝዞአል።

ስለዚህ አይሆንም አትበይ፤

ስለዚህ አይሆንም አትበይ።

ወደ ንጉሡ እየመጣህ ነው፤

ታላላቅ ልመናዎችን በፊቱ አቅርብ፤

ጸጋውና ኀይሉ እንደዚሁ ናቸውና።

ማንም ፈጽሞ ከመጠን ያለፈ መጠየቅ አይችልም፤

በጭራሽ ማንም ብዙ ሊጠይቅ አይችልም።

ጌታ በመከራችን መካከል እንዲሠራ ስንጠይቀው የሚገባውን ክብር እንሰጠዋለን።

3. ለሕዝባቸው የሚጸልዩ መሪዎችን እንድንመስል ተጠርተናል

ዕብራውያን 13፥7 ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች እንድናስብ ይነግረናል፦ “የእግዚአብሔርን ቃል የንገሯችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሏቸው።” የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ መሪዎችን ብትመረምር አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፤ ይኽውም ለጸሎት ቁርጠኛ መሆናቸው ነው። ይህንንም በሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ እንመለከታለን። እርሱና የአገልግሎት አጋሮቹ ስለ ቆላስይስ ሰዎች ከሰሙበት ቀን ጀምሮ “ስለ እናንተ መጸለይና መለመንን አላቋረጥንም” ብሎ ይነግራቸዋል (ቆላስይስ 1፥9)።

እንዴት ያለ የጽናት ምሳሌ ነው! ስለ ቆላስይስ ሰዎች ካወቀበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የማያቋርጥ ጸሎት። ወንድሞች ሆይ፣ ይህን አስቡ፤ እናም ይህን የሕይወት መንገድ ምሰሉ። በተጨማሪም የኤጳፍራን ምሳሌ እንመልከት፦ “ከእናንተ አንዱ የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነው” ጳውሎስም “እርሱም ፍጹም ጠንክራችሁና ሙሉ በሙሉ ተረጋግታችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ዘወትር ስለ እናንተ በጸሎት እየተጋደለ ነው” ሲል ይመሰክርለታል (ቆላስይስ 4፥12)። እንደ ጳውሎስና እንደ ኤጳፍራ ያሉ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸውን የጸሎት ሰዎችን ምሳሌ አስታውስ።

4. ለሕዝብህ መጸለይ የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር ያንጸባርቃል

በበዓለ ሃምሳ ቀን ላይ የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ የጸሎት መልስ ነበር። እግዚአብሔር በድንገት በኀይል ሲንቀሳቀስ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን መሪዎች፣ ከ100 ከሚበልጡ የክርስቶስ ተከታዮች ጋር፣ እየጸለዩ እና እየጠበቁ ነበር (የሐዋሪያት ሥራ 1–2)። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለ“ጸሎት” ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው ነበር (የሐዋሪያት ሥራ 2፥42)፣ ደግሞም ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትሄድ እና የመሪነት ጥያቄዎች እየጨመሩ ሲመጡ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች እንደገና ማስተካከል እንዳለባቸው ተገነዘቡ (የሐዋሪያት ሥራ 6)። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የአንዳንድ መበለቶች ችላ መባል ጉዳይ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደማይችሉ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።

ግን ትኩረታቸው ምን መሆን አለበት? በበጎነት ወይም በአስተዳደር ላይ ማተኮር አለባቸው? እነዚህ ጥሩ እና መንፈሳዊ አማራጮች ነበሩ (ሮሜ 12፥6–8)፤ ነገር ግን የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የተሻለ ነገር እንዳለ ያውቁ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ መሪነትም ይህንን አወጁ፦ “እኛ የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤ እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን” (የሐዋርያት ሥራ 6፥2-4)።

ሐዋርያቱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተናገሩትን አስተውለሃል? በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት የሚል ነው። በእርግጥ የቅዱሳን ማኅበር መበለቶችን ለራብ መተው አይችልም ነበር። መሪዎቹ ግን ጸሎትን ቢተዉ ሁሉንም ነገር እንደሚያጡ ተረድተዋል። መሪዎቹ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በመጸለይ ባልዲዎቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ጉድጓድ ውስጥ ማጥለቅ ባይቀጥሉ ኖሮ፣ መበለቶችን ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ልግስና ሁሉ ይደርቅ ነበር። የአዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲኖረን ከፈለግን የአዲስ ኪዳንን ጸሎት መረዳት እና መለማመድ አለብን።

5. ለእግዚአብሔር ሕዝብ መጸለይ፣ ሕዝቡን ወደ ለውጥ ይመራቸዋል

እንደ መጋቢ፣ ሕዝባችን ክርስቶስን በመምሰል ሲያድግ ለማየት እንናፍቃለን። ሕይወትን በሚቀይር የመጽሐፍ ቅዱስ ኀይል ስለምናምን ስብከቶችን እናዘጋጃለን። ሰዎች መሪዎቻቸውን እንደሚከተሉ ስለምናውቅ ለመንጋው ምሳሌ እንሆናለን።

ግን እንጸልያለን? ግልጽ ለማድረግ ያህል የምክር፣ የስብከት እና የሥልጠና ዕድሎች ያስፈልገናል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በጸሎት የእግዚአብሔር ኀይል ካልተለቀቀ በስተቀር ከንቱ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎትን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቅድስና ለማስቀጠል ዋነኛ መንገድ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ለዚህም ነው እንዲህ የጸለየው፦

እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ (ቆላስይስ 1፥9–11)

እውቀት፣ ጥበብ፣ ማስተዋል፣ የሕይወት ለውጥ፣ ፍሬ ማፍራት፣ ብርታት፣ ኀይል፣ ጽናት፣ እና ትዕግሥት፤ ከዚህ በላይ ምን ልትለምኑ ትችላላችሁ! ለሐዋርያው ጳውሎስ፣ እነዚህ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ በጸሎት የሚመጡ ናቸው። ዳግመኛም በፊልጵስዩስ መጽሐፍ፣ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦

ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ። ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው (ፊልጵስዩስ 1፥9–11)። ፍቅር፣ ጥልቅ ዕውቀት፣ ማስተዋል፣ ንጽሕና፣ ነቀፋ የሌለበት፣ የጽድቅ ፍሬ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና እና ክብር። በድጋሚ እነዚህ ሁሉ በረከቶች በጸሎት የመጡ ናቸው። የምናገለግላቸው ጉባኤዎች እነዚህን ባሕርያት ያሳያሉ? እኛ “ስለማንጠይቅ” (ያዕቆብ 4፥2) ምናልባትም ላያሳዩ ይችላሉ። ጌታ ሆይ እንድንጸልይ አንቀሳቅሰን!

6. ጸሎት ተራ ሰዎች ለእግዚአብሔር አስደናቂ ነገሮችን የሚያደርጉበት መንገድ ነው

ለዓመታት፣ በቤተ ክርስቲያኔ ያሉ ሽማግሌዎች በያዕቆብ 5፥14 መሠረት ለታመሙ ሰዎች ለመጸለይ ለእግዚአብሔር ጥሪ ታዛዥ ለመሆን ጥረዋል። ጌታ እንዲፈውሳቸው ለመጸለይ ከታመሙ ቅዱሳን ጋር በተሰባሰብን ቁጥር፣ በያዕቆብ መጽሐፍ ውስጥ ባለ አንድ ጥቅስ እበረታታለሁ። ያዕቆብ እንዲህ በማለት ያስታውሰናል፦ “ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር። ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል አልዘነበም” (ያዕቆብ 5፥17)። ይህንን ጥቅስ በምዕራፍ 5 መጨረሻ አካባቢ ማስቀመጡ የእግዚአብሔር ጥልቅ ርኅራኄ እንደሆነ ሁልጊዜ ይሰማኛል።

ይህን አስቡ፤ ያዕቆብ የታመሙ ሰዎች እንደሚፈወሱ ተስፋ በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ለበሽተኛ ይጸልዩ ዘንድ እንዲጠሩ ነገራቸው። ፈውስ አልፎ አልፎ እንደማይመጣ ያስባል፤ ይህም እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያኑ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንዲያደርግ መጠበቅ ያለብን ነገር ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእምነት የሚጸልይ ጸሎት የታመመውን ሰው ያድነዋል። እግዚአብሔር ያስነሣዋል” በማለት ተናግሯል። እንዴት ያለ ቃል ኪዳን ነው! ሽማግሌዎቹ እግዚአብሔር ተዓምር እንዲያደርግላቸው እየጠየቁ ነው። ያዕቆብ አንድ መጋቢ “እኔ? እኔ ተራ ሰው ነኝ!” ብሎ እንደሚያስብ ያወቃል፤ ያዕቆብ የኤልያስን ታሪክ በማጠቃለል ይህንን ተቃውሞ ይከላከላል፦  እንደገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ስጠች።” (ያዕቆብ 5፥18)።

ያዕቆብ እንዲህ እያለ ነው፦ “እነሆ ሽማግሌዎች፣ እናንተ ልክ እንደ ኤልያስ ናችሁ፣ እግዚአብሔር ለሦስት ዓመት ተኩል የአየር ሁኔታን ለመለወጥ እንደ ተጠቀመበት። በእርግጥ እግዚአብሔር እንደ እናንተ ያለ ተራን ሰው አስደናቂ ነገሮችን ለማድረግ ሊጠቀም ይችላል።” እንዴት ያለ ማበረታቻ ነው! እግዚአብሔር በአገልግሎታችን አስደናቂ ነገሮችን እንዲያደርግ ልዩ መሆን አያስፈልገንም። ይልቁንም፣ የእኛን ተራነት ሙሉ በሙሉ እና በደስታ ተቀብለን ራሳችንን ወደ አስደናቂዎቹ የእግዚአብሔር ተስፋዎች መወርወር አለብን።

ወንድሞች፣ እነዚህ ስድስት ምክንያቶች ኅሊናችሁን እንደሚቀርጹ እና ልባችሁን ወደ ጥልቅ ስሜት እና ለመጸለይ ውሳኔ እንድታደርጉ እንደሚያበረታቷችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ለሕዝባችሁ ለመጸለይ ራሳችሁን ስጡ። እግዚአብሔር አሁን ለጸሎት ወደ አዲስ ውሳኔዎች እንዲመራችሁ ለምን አትጠይቁትም? የመታዘዝ ፍሬ በእግዚአብሔር ቃል ከታደሰው አእምሮ ይውጣ (ሮሜ 12፥1-2)። ጸሎት ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጣል፤ የቀደሙትን ታላላቅ ሰዎች አርአያነት ይከተላል፤ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ የምትሰጠውን ነገር ያንፀባርቃል፤ ሕዝባችንን ይለውጣል፤ እና ተራ ሰዎች ያልተለመዱ ነገሮችን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ይጠቀምበታል። እንድንጸልይ እግዚአብሔር ይርዳን!

የአርታዒ ማስታወሻ፥ ይህ ጽሑፍ Pray for the Flock Ministering God’s Grace through Intercession (Zondervan, 2015) ከሚለው የተወሰደ ነው።

በራያን ፉለርተን