ለብዙ ሰዎች፣ ክርስቲያናዊው የመለወጥ[1] አስተምህሮ (the doctrine of Conversion) ውብ ወይም ማራኪ አይደለም። አስገዳጅ ወይም ስሜት የሚረብሽ ነው ይላሉ፤ “ማንም ሰው እምነቱን በግድ አያሰርጽብኝም!” ወይም “እምነቴና አካሄዴ ስሕተት እንደሆነ የምትነግረኝ አንተ ማን ነህ!?” ሲሉ ይስተዋላሉ።
በርግጥ በዚህ አመለካከት መሠረት ውበት እንደ ተመልካቹ ነው ሊባል ይችላል። ነገር ግን የክርስትናን አስተምህሮ በተመለከተ፣ ዋናው ነገር ማራኪ ነው ወይስ አይደለም የሚል ሳይሆን፣ እውነት ነው ወይስ ሐሰት ነው የሚል ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ እውነተኛው የክርስትና የመለወጥ አስተምህሮ እጅግ ውብ ነው።
በአንድ በኩል፣ የክርስትና መለወጥ ልክ እንደ የትኛውም ለውጥ ውብ ነው። ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ስለ አባ ጨጓሬ ወደ ቢራቢሮ መቀየር፣ ወይም የእንቁራሪት እጭ ወደ እንቁራሪትነት ስለሚለወጥበት መንገድ (Metamorphosis) ይማራሉ። በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ ይህንኑ ምስል በመጠቀም፣ በሰው ልብ ውስጥ የሚከናወነውን “በኀጢአት ሙት ከመሆን” ወደ “አዲስ ፍጥረትነት” እንዴት እንደሚለወጥ ይማሩበታል። አበባ ይፈነዳል፤ እንቁላል ይፈለፈላል፤ ጫጩትም ክንፏን ለመጀመሪያ ጊዜ ዘርግታ ትበርራለች። እነዚህ ለውጦች እያንዳንዳቸው በየራሳቸው መንገድ ውብ ናቸው፤ ሆኖም ግን በአንድነትም ውብ የሚሆኑበት መንገድ አለ። በፍጥረት ውስጥ ያሉትን የለውጥ ምሳሌዎች በመመልከት፣ ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት በመለወጥ ውስጥ የታየውን የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ መረዳት እንችላለን።
ከተፈጥሯዊው ዓለም ሕግጋቶች መካከል አንዱ፣ ለራሳቸው የተተው ነገሮች ወደ ኋላ ይመለሳሉ እንጂ አያድጉም የሚል ነው። ሁሉም ነገር ይሞታል። ሆኖም ግን እግዚአብሔር በዚህ ግዛት ውስጥ ለተሻለ ዓላማ የለውጥን ውበት እዚህም እዚያም ሰውሯል። ታዲያ እነዚህ ሁሉ የድነት ድንቅ ምልክቶች አይደሉምን?
በርግጥ መለወጥ ከዚህም ይበልጣል። ለመረዳት ከባድ ባለመሆኑ (ሮሜ 10፥9ን አስቡ) ደግሞም በውስብስብነቱ (ኤፌሶን 2፥1-10ን አስቡ) እጅግ ውብ ነው።
ነገር ግን ውብ ነው ብቻ ማለት በቂ አይሆንም። የመዳንን ውበት በጥልቀት ለማድነቅ ተጨማሪ ነገሮችን እንመልከት።
በቅንጅቱ ውብ ነው
መለወጥ የተለያዩ ክስተቶችን በውስጡ ያካተተ ውብ አሠራር ነው። መለወጥን መለወጥ የሚያሰኘው አንድ ቅጽበት አለ፦ የሆነ ወቅት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እና እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣው አናምንም ነበር፤ የሆነ ወቅት ላይ ደግሞ አምነን ተገኘን፣ ከአለማመን ወደ ማመን የመሻገር ቅጽበት።
በራሱ ጉዳይ ተጠላልፎ የነበረው ኀጢአተኛው ሰው ለማመንና ክርስቶስን በባዶ እጁ ለመያዝ የመጀመሪያውን የእምነት ውሳኔ ሲያደርግ፣ በዚያች ቅጽበት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በታቀደለት የድነት ሰንሰለት ውስጥ ይታሰራል። ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር አነጣጥሮበት የነበረው ውጤታማው ጥሪ፣ አሁን ጊዜውን ጠብቆ በተወሰነለት ጊዜ ተፈጽሟል። በሰው የታቀዱት እርምጃዎች፣ በእግዚአብሔር መሪነት አቅጣጫ ቀይረዋል (ምሳሌ 16፥9)።
በአንድ ጎኑ ከተመለከትነው፣ መለወጥ የእግዚአብሔር ዕቅድ ስኬትም የመንገዱም መነሻ ነጥብ ነው። መሠረታዊ የሆነ ውሳኔ የሚካሄድበት ቅጽበት ነው፤ ነገር ግን ከጀርባው በብዙ የታቀደለት ውሳኔም አለው። በሮሜ 8፥30 ላይ በብዙ ጥንቃቄ ስለተደረገው ስለዚህ ውሳኔ ግልጽ ማብራሪያ እናገኛለን፦ “አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው።” ዐይኖቻችን ሰዎች ንስሓ ሲገቡና በክርስቶስ ላይ እምነታቸውን ሲያሳርፉ ሊመለከቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይህንን እንዲወስኑ ያደረጋቸውን ደግሞም እስከ መጨረሻው የሚያስቀጥላቸውን ዘላለማዊ ክብር ማየት ይሳናቸዋል።
በሮሜ 8፥30 ላይ ስለ ተጠቀሱት ስለ እያንዳንዳቸው ደረጃዎች ብዙ ገጽ ሊጻፍ ይችላል። በውበት ላይ ውበትን የደረቡ ናቸው። ልቡ በተሰበረ ደካማ ኀጢአተኛ ውስጥ የተቀበረችው የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህለዋ እምነት፣ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ እግዚአብሔር በሁሉን አዋቂነቱ ይህንን ኀጢአተኛ ሰው እንዳወቀው ማሳያ ናት። ከዘላለም ዘመናት በፊት፣ እግዚአብሔር በጸጋው የዚህን ኀጢአተኛ ግለሰብ ጽኑ ዐመፃ አስቀድሞ በመመልከት፣ የተወደደ ልጅ እንዲሆን በፍቅር አስቀድሞ ወስኖታል። ከዚያም እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ኀጢአት፣ እንከን አልባ መሥዋዕት ይሆን ዘንድ አንድያ ልጁን ልኮታል። እንዲሁም በክርስቶስ ጽድቅ በማመን እርሱም ይጸድቅ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን በመላክ ደንዳና ልቡን ቀይሮለታል፤ ጻድቅ መባልም ችሏል። ታዲያ ይህ የሚደንቅ አይደለምን? ደግሞም ይህ የሚያጸድቅ የእምነት (justifying faith) ዘር፣ በአብ ታማኝነት አማካይነት የሚቀድስ እምነት (sanctifying faith) ወደ መሆን ያድጋል። በመንፈስ ቅዱስ ሥራም ወደ ክብር ተስፋ ይደርሳል። ይህም ልብን ሰርጾ የሚገባ አስደናቂ እውነት ነው።
በተስፋ ቃሉ ውብ ነው
በውስጡ ያሉት የተስፋ ቃሎች መለወጥን ውብ ያደርጉታል። ኦ፣ ያ የተስፋ ቃል! ሁላችንም ማግኘት የምንፈልገው አይደለምን? ቅዱሳንም ሆኑ ኀጢአተኞች ሁልጊዜ የሚናፍቁት ነገር ምንድን ነው? ሁሉም ሰው ለውጥን ይፈልጋል። ሁሉም ሰው መጥፎው ነገር ወደ መልካም እንዲቀየር፣ ስሕተትም ትክክለኛ መስመርን እንዲይዝ ይፈልጋል። ይህም ስለሚሳካበት መንገድ ሁላችንም የተለያዩ አሳቦች አሉን፤ በአጭሩ ግን ሁሉም ሰው የሚፈልገው ተመሳሳይ ነገርን ነው፦ ሕይወትን።
እግዚአብሔር ዘላለማዊነትን በልባችን አኑሯል (መክብብ 3፥11)። ከዚህም የተነሣ እያንዳንዱ የንቃት ቅጽበት፣ ለአንድ ወይም ለሌላ አምላክ የሚቀርብ አምልኮ መገለጫ ነው። ይህም የሰው ልጅ ትክክለኛና እውነተኛ የሆነን፣ የተወደደንና የተሻለን ተስፋ ምን ያህል እንደሚሻ ያሳያል። ብሩስ ማርሻል ታዋቂ የሆነ አባባል አለው፦ “የጋለሞታዋን ቤት በር የሚያንኳኳ ወጣት፣ ባይገባውም አምላክን እየፈለገ ነው።”[2] ይህ ታዲያ ለዝሙትም በሉት ለመንፈሳዊነት፣ ለጣዖቶቻችን ሁሉ የሚሠራ ነው። ነገር ግን ሁሉንም የሚያያይዘው እውነታ ይህ ነው፦ ለፍላጎቱ ተላልፎ የተሰጠ የትኛውም ሰው እውነተኛ የሆነውን እግዚአብሔርን አይፈልግም (ሮሜ 3፥11)። ጣዖቶቻችን አምላክ እንዲሆኑን እንፈልጋለን። እውነታው ግን እያሰስን ያለነው፣ በውድቀታችን ፈጽሞ አንፈልገውም ያልነውን ብቸኛ አምላክ ነው።
ስለዚህ “እግዚአብሔርን የሚፈልጉት” በርግጥ እግዚአብሔር ቀድሞ የፈለጋቸው ናቸው። አጽናኙም መንፈስ፣ ለሕይወት የሚያስነሣቸውን ፍለጋ ምድርን እያሰሰ ነው። እግዚአብሔር ቀድሞ ያወቃቸውን ጣዖት አምላኪዎች ይታገሣል፤ ወደ ንስሓ እንድንመጣ እንጂ ማናችንም እንድንጠፋ አይፈልግም። መንፈሱም በልባችን ውስጥ ብርሃንን ያበራል፤ ከመቃብራችንም ውስጥ፣ “ውጡ” ብሎ ይጠራናል፤ የማይታመነውም የሚታመን ይሆናል። ስለዚህም መቀየር እችላለሁ! መለወጥ እችላለሁ! እግዚአብሔርን ማወቅ እና በዚያም ሕይወትን ማወቅ እችላለሁ! የጥንቱ ዝማሬ እንደሚለው፣ “በእኔ ውስጥ ባለው የክርስቶስ ኀይል የተነሣ፣ በሕይወቴ ወቀሳ የለብኝም፤ የሞት ፍርሀትም አይዘኝም!”
ወንጌል ለእኔ እና ለዚህች ዓለም እውን የሆነውን ተስፋ ይገልጣል። የትኛውም የፍጥረት ውበት፣ ሥነ ጥበብ፣ እንዲሁም ለእድገትና ለአብርሆት የሰው ልጅ የሚያደርገው ትግል ሁሉ ተጠቅልሎ ሰው በሆነው፣ በተሰቀለው፣ በተቀበረው፣ በተነሣው እና በከበረው ኢየሱስ ውስጥ ይገኛል። እርሱ የትንሣኤ በኩራት እንደሆነው ሁሉ (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥20-23)፣ ወደ መዳን በእምነት የምንመጣበትና ለማይጠፋም ሕይወት የምንበቃበት የመለወጣችን ተስፋ ነው፤ “ሁላችንም እንለወጣለን” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥50-53)።
በእልፍ አእላፍ ሥራዎቹ ውብ ነው
መለወጥ በእልፍ አእላፍ ሥራዎቹ እጅግ ውብ ነው። ሰዎች ለድነታቸው በክርስቶስ በማመን መለወጥ ሲሆንላቸው፣ በውስጡ ከሚያካትታቸው ወሳኝ ነገሮች ሁሉ ቀዳሚው ነው። በእኔ ትውልድ ያሉ ብዙዎች “የሚድኑት” ወደ መድረክ በመምጣት፣ እጅ በመዘርጋት፣ ወይም የተቀመረ ጸሎት በመጸለይ ነው። እናም በእኔ ትውልድ ያሉ አብዛኞቹ መጋቢዎች፣ ሰዎች ለወንጌል ምላሽ እንዲሰጡ የሚደረገውን መሰል ልዩ ጥሪ አያስተናግዱም። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ወንጌል መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ መሰበኩን ሁላችንም በጥንቃቄ ማረጋገጥ ይገባናል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሚሳሳቱ ሰዎችን፣ እንከን ያለበትን መንገድ ተጠቅሞ፣ ኀያል የሆነውንና እንከን አልባውን የኢየሱስ ክርስቶስን የምሥራች ማስተላለፉ እንዴት ያለ ተዓምር ነው!
እኔ የዲስፔንሴሽናል ቅድመ መከራ ንጥቀትን የምደግፍ (dispensational pretribulational rapturist) አማኝ አይደለሁም፤ ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስ በጥበቡ እንደ “Left Behind” ዐይነት የ1970ቹ ጣፋጭ ፊልም ተጠቅሞ፣ ለምሕረት እና ጥበቃ ኢየሱስን እንድፈልግ ልቤን አለሰለሰ። ዛሬ መሰል ዘዴዎችን አልጠቀምም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልጆቹን ወደ ሕይወት ስለሚያመጣበት መንገድ ቸልተኛ ባለመሆኑ አመስጋኝ ነኝ። ደካማ በሆነው የወንጌል ስብከታችን፣ እንዲያውም እንከን ባለበት ስብከታችንና ልመናችን ፍጹም የሆነው ኀይሉ ይፈጸማል። እግዚአብሔር በወንጌል አገልግሎታችንና ከዚያም አልፎ የሚሠራበት መንገድ ሁልጊዜም ያስደንቀኛል።
ወደ ክርስቶስ የተደረጉ መለወጦች ሁሉ የመነጩት፣ እርሱን ለድነታችን እንደ ቀረበ መሥዋዕት ይዞ በመቅረብ ነው። የዚህ ግልጽ ምሳሌ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ የሳውል መለወጥ ነው። ያ ቅጽበት በጣም አስደናቂ ነው። ለአንዳንዶች ግን ቅጽበቱ ያን ያህል አስደናቂ ላይሆን ይችላል። በልጆች ቤተ ክርስቲያን (የሰንበት ትምህርት ቤት) ውስጥ አንድ ልጅ ጸሎትን ይጸልያል። አንድ ሰው በሰንበት አገልግሎት ማጠናቀቂያ ወደ መድረክ ይሄዳል። አንድ የማውቀው ሰው ደግሞ የመለወጥ ልምምድ በእርሱ ላይ ከመከሰቱ በፊት፣ በየሰንበቱ ለሦስት ዓመታት ያህል በቤተ ክርስቲያን ይመላለስ ነበር፤ በስተ መጨረሻ እንዲህ አለ፦ “መዳን አለብኝ። ማመን አለብኝ።
“That Hideous Strength” በተሰኘው ልብ ወለድ ውስጥ፣ ሲ. ኤስ. ሌዊስ በማይታበል መንገዱ፣ የአንዲትን ሴት መለወጥ መደበኛነቱን እና ክብደቱን እንዲህ አስቀምጦታል፦
እርሷን እዚያ የሚጠብቃት፣ ሐዘን እና ከዚያም ያለፈ ነው። ድምጽም ሆነ ቅርፅ አልነበረም። ከቁጥቋጦው በታች ያለው ሻጋታ፣ በመንገድ ላይ ያለው እንጉዳይ እና ትንሽ የጡብ ድንበር በሚታይ መልኩ አልተለወጡም፤ ግን ለውጥ ነበር። የድንበር ሽግግር ነበር። ወደ አንድ ሌላ ዓለም፣ ወይም ወደ አንድ አካል፣ ወይም ወደ አንድ አካል መገኘት ቀርባለች። ይህም አካል የሚናፈቅ፣ ታጋሽ፣ ፈጽሞ የማይቆም ሲሆን ያለ አንዳች መጋረጃ ወይም ከለላ ተገለጠላት…
በዚህ ከፍታ፣ ጥልቀት እና ስፋት ውስጥ “እኔ” የሚለው የራሷ ትንሽ ሐሳብ ወድቃ ጠፋች፤ ልክ አየር በሌለበት ቦታ እንዳለ ወፍ ሆነች። “እኔ” የሚለው የፍጡር ሕልውና መጠሪያ፣ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ያልነበረ ነገር ግን የሚፈለግ ፍጡር ስም መሆኑን አልጠረጠረችም ነበር። አካል ነበር (እርሷ ያሰበችው ዐይነት ባይሆንም)፤ ግን ደግሞ የተፈጠረ መሣሪያም ነበር። ሌላን (እግዚአብሔርን) ለማስደሰት እና ሌሎችን በእርሱ በኩል ደስ ለማሰኘት የተፈጠረ መሣሪያ ነበር። ያለ ምርጫው እና ባልተጠበቀ መንገድ በዚህ ወሳኝ ቅጽበት የተበጀ ነበር። ሸክላ በሚያበጁ እጆች ይሁን በመውቀጫ በየትኛው እንደሆነ እርግጠኛ ባትሆንም፣ የመፍጠር ሥራው በክብር እና በሐዘን በሁለቱ መካከል ተከናወነ።
ጊዜ ተብሎ ለመጠራት በጣም አጭር በሆነ ቅጽበት ውስጥ ትልቅ ነገር እርሷ ዘንድ ስፍራ ያዘ። እጇ ከትውስታ በቀር ምንም አልያዘም። እጇ ያለማቋረጥ ትውስታውን እንደ ያዘ፣ ከሰውነቷ ከእያንዳንዱ ክፍል ሐሴት ጠል የሆኑ ድምጾች ያንሾኳሽኩ ጀመር።
"ተጠንቀቂ። ወደ ኋላ ተመለሽ። ራስሽን ጠብቂ። ራስሽን አትስጪ” ይላሉ። ይበልጥ ደግሞ በስውር ከሌላ አቅጣጫ፣ “ሃይማኖታዊ ልምምድ ነበረሽ። ይሄ ደስ ይላል፤ ምክንያቱም ሌላው ሰው የለውም። አሁንማ የዐሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ገጣሚዎችን በተሻለ ሁኔታ መረዳት ትችያለሽ!”
. . .ሆኖም ግን መከላከያዎቿ አሁን በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ እናም እነዚህ መልሶ የማጥቃት ሙከራዎች አልተሳኩም።[3]
አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የልምምዷን ትርጉም በመለወጥ አጋንንቱ እርሷን ይቃወማሉ። ነገር ግን መላእክትም ሆኑ አጋንንቶች፣ ጄንን ከእግዚአብሔር ፍቅር መለየት አይችሉም። ስለዚህ ጸጥ ባለው የእንግሊዝ አትክልት ስፍራ፣ በተቀደሰ መሠዊያ ላይ በሚቀርቡ ጸሎቶች፣ ወይም ወንበር ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነብ ብቸኛ ነፍስ፣ ዘላለማዊነት ይወርዳል።
እግዚአብሔር ሙታንን ወደ ሕይወት የሚያመጣባቸው እልፍ አእላፍ መንገዶች ውብ ናቸው፤ አንዳንዶች አዲስ እውነታዎችን በቅጽበት ይገነዘባሉ፤ ሌሎች ደግሞ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በጊዜ ሂደት ይገነዘባሉ። አንዳንዶች መልእክቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰምተው በእምነት ምላሽ ይሰጣሉ። ሌሎች መልእክቱን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ቢሰሙም አንድ ቀን በሕይወታቸው ላይ እስኪከሰት ድረስ መንፈሳዊ ‘የሚሰማ ጆሮ’ የላቸውም። ይህ በጥበብ የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ብዙ በሆነው የሰው ልጅ ልምምድ እና የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ፣ በሚያስደንቅ እና ለየት ባለ ሁኔታ፣ ትንሣኤን እየደጋገመ አለ። የተለመደው የመለወጥ መንገድ እንኳ ያልተለመደ ነው። መላእክት ከጥቂት ዓመታት በፊት ለልጄ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኝታ ክፍልዋ ውስጥ ላሳየችው የሚያድን እምነት ያሳዩት ደስታ፣ ለጳውሎስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ካደረጉት አያንስም። እያንዳንዱ መለወጥ ተዓምር ነው። እናም ታላቁ የክርስቶስ የክብር ነጸብራቅ እኛም ውስጥ የክብር ነጸብራቅን ይፈጥራል (2ኛ ቆሮንቶስ 3፥18)።
በምንጩም ውብ ነው
መለወጥ ከምንጩ ውብ ነው። ፈጣሪ ክቡር ነውና የሚሠራው ሁሉ የከበረ ነው። እናም ከዚህ ወሳኝ እውነት የተነሣ “ውበት እንደ ተመልካቹ ነው” ማለት ብቻውን ልክ አይሆንም። ሟች በሆኑት ውስጥ ቢኖርም ባይኖርም፣ ውበት ፍጹም በሆነ መንገድ አሀዱ ሥሉስ በሆነው አምላክ ውስጥ ተሰውሯል። ዳዊት በጌታ ቤት እንዲኖር እና የጌታን ውበት ያይ ዘንድ ጠየቀ (መዝሙር 27፥4 ይመልከቱ)። ነገር ግን ጌታ እንደ እነዚህ ያሉትን ጸሎቶች ባይመልስ እንኳ፣ ውበቱ ቅንጣት ታህል አይቀንስም።
በሌላ በኩል፣ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ውበት (አብዛኛውን ጊዜ ክብሩ ተብሎ የሚጠራው) ይንጸባረቃል፤ እንዲያውም እየጨመረ ይሄዳል። ስለዚህ እግዚአብሔር ሙታንን ለአዲስ ሕይወት ካስነሣባቸው ውበቶች አንዱ፣ በስብከትና በመዝሙር ውበቱን ለማንፀባረቅ ምስጋና በተሞላ ልብ መምጣታቸው ነው (ቆላስይስ 3፥16)። ጴጥሮስ የክርስቶስን መከራና ትንሣኤ ከተመለከተ በኋላ፣ ራሱን “ሊገለጥ ባለው ክብር ተካፋይ” እንደ ሆነ አድርጎ መጥራት ችሏል (1ኛ ጴጥሮስ 5፥1)። በሚያድን እምነት ለወንጌል ጥሪ ምላሽ መስጠትን በሌላ መልኩ ካየነው፣ ያንን ውበት ማግኘት እና ያንን ማድመቅ ነው። ጳውሎስ በ2ኛ ተሰሎንቄ 2፥14 ላይ፣ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር እንድታገኙ በወንጌላችን ጠራችሁ” በማለት ጽፏል።
መለወጥ ውብ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ውብ ነው። እርሱ በክብሩ ታላቅነት እና በግርማው፣ በማንነቱ መገለጫዎች ሁሉ እና በባሕርያቱ ውብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ውበት የሚናገርበት መንገድ ራሱ ዉብ ነው። ይህም በአምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ትረካዎች ከቀረቡት ቅድስናዎች አንሥቶ እስከ መዝሙራት ድረስ፣ እግዚአብሔር ለኢዮብ ከመለሰለት አስደናቂ መልስ አንሥቶ እስከ ነቢያት ድንቆች፣ ከወንጌላት አንሥቶ በመልእክቶች እስካሉት የላቁ መደነቆች፣ ከመለኮታዊ ማወደሶች በዮሐንስ እስካሉት አወዛጋቢ ራእዮች ድረስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ጥልቅ እና አስደናቂ ውበቶች ተውቧል።
እናም ይሄ አስደናቂ፣ ቅዱስ እና ከአእምሮ በላይ የሆነው እግዚአብሔር፣ አወቀን፤ ወደደን፤ መረጠን፤ ጠራን፤ እናም አዳነን። “በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቶአልና” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥6)። የመለወጥ ውበት (ገና ደግሞ ለዘላለም የምንመረምረው) ሁሉ፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር ውበት የመነጨ እና የእርሱ ጥላ ነው፤ ክብሩንም እንድናየው እና ኢየሱስን በማወቅ ለዘላለም እንድንለወጥ፣ ክብሩ በጊዜ ሳይገደብ ይገለጣል።
በጃሬድ ዊልሰን
[1] Conversion ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።
[2] Bruce Marshall, The World, The Flesh and Father Smith (Boston: Houghton Mifflin, 1945), 108.
[3] C.S. Lewis, That Hideous Strength (New York: Macmillan, 1970), 318-319.