ከታች የተዘረዘሩት ዐሥር ነጥቦች፣ በካልቪኒዝም አምስቱ ነጥቦች ማመን ስላለው በጎ ተጽእኖዎች የግል ምስክርነቴ ነው። በቅርቡ በዚህ ርዕስ ላይ ሴሚናር አስተምሬ ስጨርስ፣ የሴሚናሩ ተካፋዮች እነዚህን የግል ምስክርነቶች እንዲያገኙት በማሰብ በበይነ መረብ ላይ እንድለጥፈው ጠየቁኝ። እኔም ያንን ለማድረግ ደስተኛ ነኝ። እነርሱ በርግጥ የትምህርቱን ይዘት ከ Desiring God Ministries ድህረ ገጽ ላይ የሚገኘውን ይወስዳሉ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እኔ “ካልቪኒዝም” የምለውን አስተምህሮ ያስተምር እንደ ሆነ እንደ ቤርያ ሰዎች ይመረምሩ ዘንድ ተስፋ በማድረግ ለሌሎች እዚህ እጽፍላቸዋለሁ።
- እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔርን እንድፈራ እና እውነተኛና እግዚአብሔርን ማዕከል ወዳደረገ ጥልቅ አምልኮ ይመሩኛል
በ70ዎቹ መገባደጃ ላይ ኤፌሶንን በቤቴል ኮሌጅ እያስተማርኩ፣ የእግዚአብሔርን ሥራ አጠቃላይ ግብ የሚገልጠውን ሐረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት አስታውሳለሁ። ሐረጉም፣ “የጸጋው ክብር ይመስገን ዘንድ” የሚል ነበር (ኤፌሶን 1፥6)።
ይህ ክፍል እግዚአብሔርን ማገዝ እንደማንችልና ክብሩ የበለጠ የሚያበራው የእርሱን ፍላጎቶች ለማሟላት ስንጥር ሳይሆን የድርጊቶቻችን ሁሉ መሠረት ሆኖ በእርሱ ስንረካ መሆኑን እንዳስተውል አድርጎኛል። “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነው፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን” (ሮሜ 11፥36)። አምልኮ በራሱ የመጨረሻ ግብ ይሆናል።
ይህ እውነት ፍቅሬ ምን ያህል ዝቅተኛ እና በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማኝ አድርጓል። ይህም በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ያሉትን ጥልቅ ጌታን የመፈለግ መዝሙሮች ይበልጥ እንድረዳቸዉ በማድረግ የማምለክ ጥማቴን ጨምሮልኛል።
- እነዚህ እውነቶች መለኮታዊ ነገሮችን ከማቃለል ይጠብቁኛል
ባህላችን መጥፎ ከሆነበት ነገር አንዱ አስመሳይነትን፣ ተፈላጊ የመሆን ጥማትን እና የስኬት ሕይወትን ማራገቡ ነው። ቴሌቪዥን ደግሞ የዚህ የአስመሳይነት እና የከንቱነት ሱሳችን ዋና መጋቢ ነው።
እግዚአብሔር በዚህ ባህል ውስጥ ተውጧል። ስለዚህም መለኮታዊ ነገሮች ይቃለላሉ።
በዘመናችን ትጋትና ቁም ነገረኝነት ብዙ የለም። ምናልባት ሚዛን የሳቱ አንዳንድ ሰዎች ዘና ለማለት እና ስለ አየር ሁኔታ ለማውራት እንኳ ጊዜ የሌላችው በጥድፊያ የተሞሉ ይኖሩ ይሆናል።
ሮበርትሰን ኒኮል ስለ ስፐርጅን ሲናገር፣ “አስቂኝ መልክ ያለው የወንጌል ስርጭት ብዙዎችን ሊስብ ይችላል፤ ነገር ግን ነፍስን በአዘቅት ውስጥ ያስቀምጣል፤ እናም የእምነትን መሠረት ይንዳል። ሚስተር ስፐርጅን ብዙ ጊዜ ስብከቱን የማያውቁ ቀልደኛ ሰባኪ እንደሆነ ያስባሉ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ እርሱ ያለ ድምጹ ወጥ የሆነ ክብደት ያለው፣ ቁም ነገረኛ እና ቅን ሰባኪ አልነበረም።” (Quoted in The Supremacy of God in Preaching, p. 57)
- እነዚህ እውነቶች፣ በራሴ ድነት እጅግ እንድደነቅ ያደርጉኛል
በኤፌሶን 1 ላይ እግዚአብሔር ያደረገውን ታላቁን ማዳን ካስቀመጠ በኋላ፣ ጳውሎስ በዚያ ምዕራፍ የመጨረሻ ክፍል ላይ እንዲህ ይጸልያል፦ የዚህ ነገረ መለኮት ውጤት የልባችን ዐይኖች በርተው በተስፋችን፣ በርስታችን ክብር ባለጠግነት እና በእኛ ውስጥ በሚሠራው የእግዚአብሔር ኀይል እንድንደነቅ ነው። ይህም ኀይል ሙታንን የሚያስነሣ ኀይል ነው።
እያንዳንዱ የትምክህት መሠረት ተወግዷል። ከተሰበረ ልብም ደስታ እና ምስጋና ይፈልቃል።
እግዚአብሔርን መምሰል ማደግ ይጀምራል። እግዚአብሔር የራሱን ግርማና የእኛን ክፋት ሲያሳየን፣ ያኔ የክርስትና ሕይወት ከተለመደው የቅድስና መንገድ የተለየ ይሆናል። ኤድዋርድስ እንዲህ ሲል በሚደንቅ ሁኔታ ገልጾታል፦
የቅዱሳን መሻት ምንም እንኳ ጠንካራ ቢሆንም የትሕትና መሻት ነው። ተስፋቸው ትሑት ተስፋ ነው። ደስታቸውም በቃላት የማይገለጽ እና በክብር የተሞላ ቢሆንም ትሑት ከተሰበረ ልብ የሚወጣ ደስታ ነው። ደግሞም ክርስቲያኖችን የበለጠ በመንፈስ ድኾች እንዲሆኑ እና እንደ ትንሽ ልጅ ዝቅ የማለትን ባሕርይ እንዲላበሱ የሚያደርግ ነው። (Religious Affections, New Haven, Yale University Press, 1959, pp. 339f)
- እነዚህ እውነቶች ወንጌሉን ከሚመስሉ፣ ሰው ተኮር ትምህርቶች እንድጠነቀቅ ያደርጉኛል
በመጽሐፌ “The Pleasures of God” (2000) ከገጽ 144-145 በ18ኛው ክፍለ ዘመን በኒው ኢንግላንድ ከእግዚአብሔር ሉዓላዊነት አስተምህሮ መንሸራተት ወደ አርሚኒያኒዝም እና ከዚያም ወደ “ሁሉም ሰው ይድናል” (universalism)፣ በመጨረሻም ደግሞ ሥላሴን ወደ መካድ (Unitarianism) እንዴት እንዳመራ አሳይቻለሁ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከስፐርጅን በኋላ በእንግሊዝ ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል።
ኢየን መሪይ Jonathan Edwards፥ A New Biography (Edinburgh፥ Banner of Truth, 1987) በሚለው መጽሐፉ ገጽ. 454 ላይ ተመሳሳይ ነገር አስቀምጧል፦ በሰሜን አሜሪካ የካልቪኒዝም መረዳት እየቀነሰ ሄደ። ኤድዋርድስ በትክክል እንደጠበቀው የውድቀት ሂደት፣ ከታላቁ መነቃቃት በኋላ አርሚኒያኒዝምን የተቀበሉት የኒው ኢንግላንድ ጉባኤያት አብያተ ክርስቲያናት ቀስ በቀስ ሥላሴን ወደ መካድ ዩኒታሪዝም (Unitarianism) እንዲሁም “ሁሉም ሰው ይድናል” (universalism) በቻርለስ ቻውንሲ መሪነት ተቀበሉ።
እንዲሁም በJ.I. Packer’s Quest for Godliness (Wheaton, IL፥ Crossway Books, 1990) ገጽ. 160 ላይ ሪቻርድ ባክስተር እነዚህን ትምህርቶች እንዴት እንደተወ እና የሚቀጥሉት ትውልዶች በኪደርሚንስተር በሚገኘው የባክስተር ቤተ ክርስቲያን እንዴት አስከፊ ፍሬ እንዳጨዱ ማንበብ እንችላለን።
እነዚህ አስተምህሮዎች፣ ከውጭ ጠንካራና ተወዳጅ መስለው ከውስጥ ግን ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ቀስ በቀስ ከሚያበላሹ እና ከሚያደክሟት ሰውን ማዕከል ካደረጉ አስተምህሮዎች ራሷን የምትከላከልበት ምሽግ ናቸው።
“ቤቱም የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው” (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥15)።
- እነዚህ እውነቶች በዓለማዊነት በተዋጠውና እግዚአብሔርን በሚያሳንሰው ባህላችን እንዳዝን ያደርገኛል
እግዚአብሔር እንደ ጎደለ ሳይሰማኝ ጋዜጣ ማንበብ፣ የቲቪ ማስታወቂያ ወይም ቢልቦርድ ማየት ይከብደኛል።
እግዚአብሔር በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ዋናው እውነታ ሆኖ ሳለ እንደሌለ በመቆጠሩ እየተከማቸ ያለውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ሳስብ እፈራለሁ። እደነግጣለሁ! ብዙ ክርስቲያኖች ከዓለም ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማስታገሻ መድኀኒት ይወስዳሉ። ነገር ግን እነዚህ የካልቪኒዝም ትምህርቶች ትልቅ መድኀኒት ናቸው።
እናም ለመነቃቃት እና ለተሐድሶ እጸልያለሁ።
በተጨማሪም እግዚአብሔርን በሁሉም ቦታ እና ሁል ጊዜ የሚያሳዩ በእግዚአብሔር የተሞሉ ሕዝቦች እንዲፈጠሩ ለመስበክ እሞክራለሁ።
እኛ የምንኖረው የእግዚአብሔርን እውነታ እና በሁሉም ሕይወት ውስጥ ያለውን ልዕልና እንደገና ለማረጋገጥ ነው።
- እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔር ያቀደው እና የጀመረው ሥራ፣ በዓለም አቀፍ እና በግል ደረጃ እንደሚጨርሰው እንድተማመን ያደርጉኛል
የሮሜ 8፥28-39 ነጥብ ይህ ነው።
እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው።
ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
- እነዚህ እውነቶች ሁሉንም ነገር በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማዎች ውስጥ እንዳይ ያደርጉኛል፦ ሁሉም ነገር ከእርሱ በእርሱ እና ለእርሱ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ለእርሱ ይሁን!
ሕይወት ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የተያያዘ ነው። እርሱ በጣም አስፈላጊ ያልሆነበት ክፍል የለም። እርሱ ለሁሉም ነገር ትርጉም የሚሰጥ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31)።
የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ሲሰራ ማየቴ እና ጳውሎስ፣ “ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው” ሲል መስማት ዓለምን በዚህ መንገድ እንድመለከት አድርጎኛል (ኤፌሶን 1፥11)።
- እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔር ሰዎች እንዲለወጡ የሚደረግ ጸሎትን እንደሚመልስ ተስፋ እንዳደርግ ደግሞም ይህንን ጸሎት የመመለስ ፈቃድ፣ መብት እና ኀይል እንዳለው እንዳውቅ ያደርጉኛል
የጸሎት መሠረት የእግዚአብሔር ጣልቃ መግባትና የሰዎችን ልብ ጨምሮ ሁሉንም ነገሮችን መለወጥ መቻሉ ነው። የሰውን ፈቃድ መቀየር ይችላል። “ስምህ ይቀደስ” ማለት ሰዎች ስምህን እንዲቀድሱ አድርግ ማለት ነው። “ቃልህ ይሩጥ ይከበርም” ማለት ልቦች ለወንጌል ክፍት ይሁኑ ማለት ነው።
የአዲስ ኪዳን ተስፋዎች በልጆቻችን፣ በጎረቤቶቻችን እና በሁሉም የዓለም የተልእኮ መስኮች መካከል እንዲፈጸሙ እግዚአብሔርን መለመን አለብን።
“እግዚአብሔር ድንጋዩን ልብ ከውስጣቸው አውጣ፤ ሥጋ ልብም ስጣቸው” (ሕዝቅኤል 11፥19)
“አምላክ ሆይ! ይወዱህ ዘንድ ልባቸውን ግረዝ” (ዘዳግም 30፥6 )
“አባት ሆይ! መንፈስህን በውስጣቸው አሳድር እናም በሥርዐትህ እንዲሄዱ አድርግ” (ሕዝቅኤል 36፥27)
“ጌታ ሆይ ከዲያብሎስ ወጥመድም ያመልጡ ዘንድ ንሰሓንና እውነትን ማወቅ ስጣቸው” (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥ 25-26 )
“አባት ሆይ በወንጌሉ ያምኑ ዘንድ ልባቸውን ክፈት” (የሐዋርያት ሥራ 16፥14)
- እነዚህ እውነቶች ሰዎች ወደ ክርስቶስ መጥተው እንዲድኑ የወንጌል ሥርጭት ፍጹም አስፈላጊ እንደሆነ፣ ደግሞም ሰዎችን ወደ እምነት መምራት ትልቅ የስኬት ተስፋ እንዳለው ያስታውሰኛል። ነገር ግን ለውጥ በመጨረሻ በእኔ ወይም በማያምነው ሰው ጠንካራነት ላይ የተመሠረተ አይደለም
ስለዚህ ለስብከተ ወንጌል ተስፋን ይሰጣል፤ በተለይም በከባድ ቦታዎች እና ሕዝቦች መካከል።
“ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ” (የዮሐንስ ወንጌል 10፥16)።
ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ራሳችሁን ወደ ሥራው በሙሉ ልብ አስገቡ።
- እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔር በመጨረሻ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ እንድሆን ያደርጉኛል።
ኢሳይያስ 46፥9-10 የጥንቱን፣ የቀደመውን ነገር አስታውሱ፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም። የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።
ሁሉንም በአንድነት ስናስቀምጠው፣ እግዚአብሔር ይከብራል፤ እኛም እንደሰታለን።