ስለ አማሟታችሁ ዕቅድ ከሌላችሁ፣ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት የሆነ ሰው ምናልባት ቴሌቪዥን ሊከፍትባችሁ ይችላል።
የእግዚአብሔር ቃል አገልጋይ እንደ መሆኔ፣ ሰዎች በደኅና እንዲሞቱ መርዳት የጥሪዬ አካል ነው ብዬ ሁልጊዜ አስባለሁ። ያም ክርስቶስ በሥጋው ሞት አማካይነት በሰውነቱ እንዲከብር ጳውሎስ ያለውን ዓላማ የሚያጠቃልል ነው (ፊልጵስዩስ 1፥20)። የእያንዳንዱን እሁድ ስብከት፣ የዚህ ለሞት የመዘጋጀት አካል አድርጌ አስበዋለው። ደግሞም በሟች አልጋ አጠገብ የሚደረግ እያንዳንዱ ጉብኝት እምነትን የሚያጠነክር፣ ተስፋን የሚሰጥ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተሞላ፣ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ እና ክርስቶስን የሚያልቅ እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
ለዚህም ነው የሞት ጨለማ በቀረበበት ሆስፒታል ውስጥ የሚጮኽን ቴሌቪዥን በማየቴ እጅግ ያዘንኩት። ይህ ፍፁም የማይመስል ነገር ነበር። እንግዳ ነገር ነው!
እስከዛሬ ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን እጅግ የምትፈራ አንዲት እኅት ለሞት ተቃርባ ነበር። በመንፈስና በጸሎት የተሞላች ነበረች። በመጨረሻ ቀናቶቿ ልጎበኛት ወደ ሆስፒታል በሄድኩበት ጊዜ፣ ሞቷ እንዲፈጥንላት እንድጸልይላት እየተማፀነች፣ ሌሊት ላይ የምታየውን ቅዠት ነገረችኝ፤ “ግማሽ ራቁት ሴቶች በአልጋዬ ዙሪያ ሲጨፍሩ አያለሁ” አለችኝ። ምናልባት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ከከፈቱት ቴሌቭዥን ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆን ብዬ አስባለሁ።
ምናልባትም ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በርግጠኝነት ሁላችንም የምንስማማበት ነገር፣ “የፈራጁን እና የፈጣሪያችንን ፊት ያለ ፍርሀት ለማየት” ነፍሳችንን የምናዘጋጅበት የተሻለ መንገድ አለ። በደኅና የመሞት ዕቅድ አንዱ አካል፣ ለክርስቶስ ክብር እንዴት መኖር እና መሞት እንደምትፈልጉ ያላችሁን ራእይ የሚጋሩ ጓደኞችን ማግኘት ነው። አብዛኞቻችን የሞታችን የመጨረሻ ቀናት እና ሰዓታት ላይ፣ ይህንን ለማዘጋጀት በአእምሮም ሆነ በአካል በጣም ደካማ እንሆናለን። ስለዚህ ካሁኑ ብንዘጋጅ የተሻለ ነው።
ሽማግሌም ሁኑ ወጣት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሞላበት፣ ወንጌልን ያማከለ ሞት እንደምትፈልጉ፣ ብሎም እንደሚያስፈልጋችሁ ይታወቅ። ይህንን ስል ጆን ኖክስ የመረጠውን የሞት ዐይነት እያሰብኩ ነው።
የኖክስ “የመጀመሪያው መልሕቅ”
እ.ኤ.አ. ሕዳር 18፣ 1565 ዓ.ም ላይ ኖክስ የ57 ወይም 58 ዓመት ሰው ነበር (የተወለደበት ዓመት ርግጥ አይደለም)። በብሮንካይተስ የሳምባ ምች ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የጄን ዳውሰን ኒው ባዮግራፊ የተሰኘው መጽሐፍ የመጨረሻ ቀናቶቹን እንዲህ ይዘግባል።
ሚስቱ ማርጋሬት፣ ሦስት ሴት ልጆቻቸውን እና ሁለት ወንድ ልጆቻቸውን መንከባከብ ትታ ከጎኑ አትለይም ነበር። የኖክስ ታማኝ ጸሐፊ እና ጓደኛ የሆነው ሪቻርድ ባናታይንም ከአልጋው አጠገብ ፈጽሞ አይርቅም ነበር።
ከአመሻሹ 11 ሰዓት አካባቢ ሚስቱን ጠራ። ከዚያም ጊዜ አስቀድሞ በጣም ጣፋጭ የሆነውን ኢሳይያስ 53 ላይ ያለውን የወንጌል ቃል እንዲነበብለት ጠይቆ ነበር፦
ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤
ስለ በደላችንም ደቀቀ፤
በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤
በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤
እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤
እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል
በእርሱ ላይ ጫነው።
እንዲሁም 1ኛ ቆሮንቶስ 15ን፣ በክርስቶስ እና በእርሱ ትንሣኤ መካከል ያለውን ግንኙነት በጥልቅ ከሚያስረዳው ማብራሪያው ጋር አብሮ እንዲነበብለት ጠይቆ ነበር።
በመጨረሻ ግን ሚስቱን፣ የሚወደውን “የመጀመሪያ መልሕቁ” የሆነውን ዮሐንስ 17ን እንድታነብለት ጠየቃት። ከሠላሳ ዓመታት በፊት ኖክስ ከሮማ ካቶሊካዊነት ወደ ተሐድሶ እምነት በመጣ ወቅት፣ ሰላምን የሰጠው ይህ ምዕራፍ ነበር። እርሱም፣ “የመጀመሪያውን መልሕቅ የጣልኩት እዚህ ላይ ነው” ይላል። በዚህም ክፍል ላይ አስቀድሞ የመመረጡን ሥር መሠረት እና አብ ለክርስቶስ የሰጠውን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት አይቷል።
“ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። . . . እነርሱ የአንተ ስለሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። . . . ቅዱስ አባት ሆይ፤ . . . በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። . . . የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። . . . ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው።”
ማርጋሬትም መልሕቅ የሆነለትን ምዕራፍ አነበበችለት። ኖክስም እንዲህ አለ፤ “ይህ የሚያጽናና ምዕራፍ አይደለምን?” ከስድስት ሰዓታት በኋላም ሞት መጣ።
ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ እንደ ተኛ በማሰብ፣ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ የተለመደውን የምሽት ጸሎታቸውን እያደረጉ ነበር። ዶ/ር ፕሬስተን መዝሙረ ዳዊት ሲነበብለት፣ ሲዘመርለት እና ሲጸለይለት ሰምቶ እንደ ሆነ ሲጠይቀው፣ ኖክስ እንዲህ ሲል መልሷል፤ “እኔ የሰማኋቸውን ያክል እናንተ እና የሰው ዘር ሁሉ ሰምቶት ቢሆን እያልኩ እመኛለሁ። እናም የሰማያዊ ዜማ አምላክን አመሰግናለሁ።” ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢም፣ ሮበርት ካምቤል በአልጋው አጠገብ ባለው በርጩማ ላይ ተቀምጦ፣ ኖክስ በረጅም ተንፍሶ፣ “አሁን ተፈጸመ” ሲል ሰምቶታል። ኖክስ የክርስቶስን ተስፋዎች እንደሚያስታውስ ለማወቅ ምልክቱን እንዲያሳይ ባናታይን ሲጠይቀው፣ ኖክስ እጁን ለመጨረሻ ጊዜ አንሥቶ “ያለምንም ሕመም አንቀላፋ”። የኖክስ ጦርነት አበቃ።
(Knox፤ ገጽ 310)
አዎን፤ ጦርነቱ እስከ መጨረሻው የተካሄደው በእግዚአብሔር ቃል ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተሞላ ሞት ነበር። የጠየቀውም ይህንን ነበር፤ ሚስቱና ጓደኞቹም የሰጡት ይህንኑ ነው።
ለመንግሥተ ሰማይ ዝግጁ መሆን
ሞቴ ቀስ ብሎ ከመጣ ለመስማት ተስፋ የማደርገው የእግዚአብሔር ቃል ሲዘመር እና ሲሰበክ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ እና የወንጌልን እውነት መዘመርን ወድዳችሁ የማታውቁ ከሆነ፣ እነዚህን የኖክስን ቃላት በጥልቀት አሰላስሏቸው፤ “ያንን የሰማያዊ ዜማ አምላክ አመሰግናለሁ።”
በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ከቴሌቪዥን ድምጽ የበለጠ የሚረብሽ ነገር አይኖርም። እንዲሁም ደግሞ “የሰማይ ዜማ” የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ከሚዘምሩ እና ከሚያነቡ ጓደኞች የበለጠ ጣፋጭ ነገር አይኖርም። በወንጌል የተሞላ፤ በክርስቶስ የተሞላ፤ በተስፋ የተሞላ። ዕቅዳችሁ ይሄ ይሁን።
በጆን ፓይፐር