በሥራ ቦታ ወንጌልን መስበክ

በክርስትና ላይ የባህል ተቃውሞ እጅግ እየጨመረ በሄደ ቁጥር፣ በሥራ ቦታ የወንጌል አገልግሎትህ ላይ ያለው ተጽእኖ ምንድን ነው? ይህ የበለጠ ታማኝ ወይስ የበለጠ ፈሪ አድርጎሃል?

የበለጠ ብትፈራ ብዙ ልትወቀስ አይገባህም፤ ምክንያቱም የማኅበራዊ ለዘብተኝነት መስፋፋት እና የሰው ኀይል አመራር ፖሊሲዎች የሥራ ቦታ “መቻቻልን” ያበረታታሉ። ከዚህም የተነሣ ማኅበራዊ ሽኩቻን እና ከሥራ እንደ መባረር የመሳሰሉትን መዘዞች በመፍራት፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን ወንጌል ላለማካፈል በተለምዶ የምንጠቅሳቸው ፍርሃቶች ናቸው።

ወንጌልን መስበክ መቼም ቢሆን አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም። ዛሬ ዛሬ በሚገጥሙን ፈተናዎቻችን ዙሪያ አዲስ ነገር አለ ከተባለ፣ የተቃዋሚዎቻችን ድፍረት ነው። ከዚህ በፊት ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች፣ “ሁሉም ያሻውን መንገድ ይከተል” ይሉ ነበር። አሁን ግን እነርሱ እኛን በአብዛኛው ጊዜ በኋላ ቀርነት ሊፈርጁን ይወዳሉ፤ “የምር፣ በዝግመተ ለውጥ (Evolution) አታምንም?” ወይም ደግሞ፤ የጥላቻ አቀንቃኝ አድርገው ያዩናል፣ “እንዴት ግብረ ሰዶማዊነት ኀጢአት ነው ትላለህ?” አሠሪዎች የቅጥር እና የዕድገት ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት የተቀጣሪውን የማኅበራዊ ሚዲያ ውሎ ጥልቅ ፍተሻዎችን ማድረግ ጀምረዋል።

ኩባንያዎች የክፍፍል እና የመድሎን ወሬ በመፍራት ለቦታው ተገቢ የሆነን እውነተኛ ክርስቲያን ቦታውን በማይመጥን ሌላ አማኝ ባልሆነ ሰው መተካትን መቼ ነው የሚያቆሙት? ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ከሰው በላይ እግዚአብሔርን በመፍራት ወንጌል ያካፈሉኝን ወንድሞች በጣም አመሰግናለሁ። የራሴ ድነት፣ የሥራ ቦታ ምስክርነት ፍሬ ነው።

ጠፍቶ የነበረ፣ በሥራ ቦታ ላይ የተገኘ

ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ አማካሪ ድርጅት ውስጥ ተመራማሪ ነበርኩ። በራስ የሚተማመን፣ የማንንም እርዳታ የማይፈልግ፣ በሙያ የበለጸገ ሂንዱ ነበርኩ። በመንፈሳዊ ጉዳይ ላይ እርግጠኛ የሆነ ሰው ነው ብለህ ልታስብ ትችል ይሆናል። በእውነቱ ከሆነ፣ ስለ መንፈሳዊ ነገር እርግጠኛ እንዳልሆንኩ እኔም ብሆን አላውቅም ነበር። ክርስቶስን በንቃት የሚፈልግ ሰው እንዳልነበርኩ ግን አውቃለሁ።

ክርስቲያን ባልደረባዬ ሃንተር በቢሮው አካባቢ ታዋቂ እና በጣም የተወደደ፣ ከፍተኛ የሽያጭ ሰራተኛ ነው። አንድ ሰው፣ “እርሱ ክርስቲያን ነው፤ ያስታውቃል!” አለኝ። ያ ምን ማለት እንደሆነ በዝርዝር ሁለታችንም አናውቅም ነበር። ሃንተር በአእምሮዬ ከሳልኩት የክርስቲያን ስዕል ጋር እንደማይገጥም አውቃለሁ። ክርስቲያኖች ጨዋ፣ ፋራ፣ ግብዞች፣ እና ደባሪ ሰዎች አድርጌ ነበር የማያቸው። ሃንተር ግን እንዲህ አልነበረም። ስለዚህ እሱን መከታተል ጀመርኩ።

ጓደኛሞች ሆንን። አብረን ጊዜ ማሳለፍ ጀመርን እናም ስለ ሲምፕሰንስ፣ ሎርድስ ኦፍ ዘ ሪንግ ፣ ክርስቶስ፣ ክሪሽና፣ ቡና፣ ሥራ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተጨዋወትን። ጌታ እኔን ለማግኘት ሀንተርን ሲጠቀም፣ እንደ ጓደኛ እንጂ እንደ የፕሮጀክት የሥራ ባልደረባ ተሰምቶኝ አያውቅም። እግዚአብሔር ብቻ በሚያደርገው ሉዓላዊ ጣልቃ ገብነት፣ እግዚአብሔር በሕይወቴ ውስጥ መንፈሳዊ ቀውስ ባቀናበረበት በዚያ ጊዜ ሃንተር እንዲገኝ አደረገው። እናም ሃንተር በእኔ ሕይወት ውስጥ በሚያስፈልገኝ ጊዜ እውነትን እንዲናገር ጌታ ጥበብ እና ድፍረት ሰጠው።

የሥራ ቦታ ወንጌላዊ ባሕርያት

በጊዜው በእምነቱ ገና ወጣት የነበረ ቢሆንም፣ የትኛውም አማኝ በሥራ ቦታው ሊተገብረው የሚችለው ከሃንተር የምንማረው ብዙ ምሳሌዎች አሉ።

1. የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን በግልጽ ሆኔታ አሳውቅ

በመጀመሪያ ክርስቶስን ከፊት ለፊት አድርገው። በሥራ ቦታ ሌሎች ክርስቲያኖችን ማግኘት ብርቅ ሊሆን ስለሚችል፣ በቢሮው ውስጥ ያሉ ሰዎች የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን እንዲያውቁ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ እራስህን ለደካማ አማኞች እና ለማያምኑት ሰዎች ምሳሌ ማድረግ ትችላለህ። ስለ ሃንተር እምነት የነገረኝ ክርስቲያን ያልሆነ የሥራ ባልደረባዬ ነበር። ይህንን በግብዝነት ወይም ኀላፊነት በጎደለው መልኩ ማድረግ የለብንም። ነገር ግን የሰንበት ውሎህን በማውሳት፣ ያለህበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመግለጽ ወይም ለሌሎች እንዴት እንደምትጸልይ ብታካፍል ሰዎች ያኔ በቀላሉ ማን እንደሆንክ ያውቃሉ።

2. ከልሕቀት ጋራ ሥራህን ሥራ

ሁለተኛ፣ በልሕቀት ሥራ። ክርስቶስን ከፊት ስታደርገው እኔ ሃንተርን እንዳጠናሁት በባልደረቦችህ እንደምትጠና ጠብቅ። የእግዚአብሔርን ፈጠሪነት፣ ዓላማ እና መልካምነት በሚያንፀባርቅ መንገድ ሥራህን ሥራ። ታማኝነትን እና ቅንነትን አሳይ። “ሳታጉረመርም ወይም ሳታማርር” ሥራ (ፊልጵስዩስ 2፡14)። በሥልጣን ላይ ላሉት ተገዛ፣ በትሕትና አገልግል።

ይህ በራሱ የወንጌል ምስክርነት አይደለም፤ ነገር ግን በሥራ ላይ ያለን የሕይወታችን ሁኔታ፣ የምናካፍለውን የወንጌል ይዘትን ማዳከም ሳይሆን ማጠናከር አለበት።

3. ባልደረቦችህን ውደድ

ሦስተኛ፣ ባልደረቦችህን ውደድ። በሥራ ቦታህ ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ባለህ ወዳጅነት ከልብ ሥራበት። እንደ “የፕሮጀክቶች” ባልደረባ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠሩ ሰዎች አድርገህ ውደዳቸው። የመተማመንን አስፈላጊነት አቅልለህ አትመልከት። እኔ እና ሃንተር መጽሐፍ ቅዱስ አብረን ያጠናነውና እግዚአብሔር ለወንጌል የሚሆን ጆሮን የሰጠኝ ከተገናኘን ከአንድ አመት ተኩል በኋላ እንደሆነ ይሰመርበት።
የምሳ ዕረፍትህን አስልተህ ተጠቀም። በምትችለው መጠን፣ የእራስህን ሕይወት ማጋራት በምትችልበት መንገድ ለጋስ ሁን። ከቢሮ ውጪ ባሉት ቦታዎች ለመገናኘት ዝግጁ ሆን።

4. ወንጌልን ለመስበክ ተዘጋጅ

አራተኛ፣ ወንጌልን ለመስበክ ተዘጋጅ። ይህ ሞኝነት ቢመስልም፣ ወንጌልን በቀላሉ እንዴት ማስረዳት እንዳለብህ እርግጠኛ ሁን። ካስፈለገህ ተለማመደው።

ጌታ እድል ሲሰጥህ፣ ግልጽ ስላላደረከው ማብራሪያ ውስጥህ እንዲወቅስህ አትፈልግም፤ ይልቁንም የሥራ ባልደረባህን እና ለመረዳት የሚቸግረውን ጉዳይ ለማዳመጥ አእምሮህ ነጻ እንዲሆን ትፈልጋለህ። ደግሞም የሚያድነው ወንጌል እንጂ ፈጣን ማስተዋል እና ዕቅበተ እምነት አይደለም። ስለ ሃንተር ግልጽነት፣ ድፍረት እና በወንጌል ኀይል መታመን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።

5. ጸልይ

አምስተኛ፣ ጸልይ። ለሥራ ባልደረቦችህ አዘውትረህ ጸልይ። ወንጌልን ለማካፈል መልካም አጋጣሚዎችን ለማግኘት ጸልይ። በድፍረት እንድታድግ ጸልይ። እግዚአብሔር ትልቅ እና ሰው ትንሽ ሆኖ እንዲታይህ ጸልይ፤ ብዙውን ጊዜ ሁለቱን በማቀላቀል ሁላችንም ተወቃሾች ነን።

እናም በቤተ ክርስቲያንህ ያሉ ወንድሞች እና እኅቶችም እንዲጸልዩ ጋብዛቸው። በኋላ ሃንተር የእርሱ የወንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ስለ ክርስትና እምነቱ ከጠየቅኩት ጊዜ ጀምሮ እየጸለዩልኝ እንደነበር ነገረኝ።

ስለ ታማኝነት የቀረበ ጥሪ

የሥራ ቦታዎች ለክርስትና የበለጠ ጥላቻ እያሳደጉ ሲሄዱ፣ እነዚህ ያየናቸው መሠረታዊ ልማዶች ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናሉ። ብዙ ጥሩ እድሎችን ለማግኘትና የምናገረውን ቃላት እንዲሰጠኝ የጸለይኩትን ጸሎት ጌታ ለመመለስ ቸር ነው። ክርስቲያን በመሆኔ በመታወቅ፣ በሙያዊ እና በማኅበራዊ ዘርፍ እምነቴን በመኖር እና ባልደረቦቼን እንደ እግዚአብሔር አምሳል የበለጠ መውደዴ ስለ እምነቴ በግልጽ ለመናገር እድሎችን ሰጥተውኛል። እናም በአስደናቂ ጸጋው፣ አንድን ባልደረባ ወደ እምነት ለማምጣት እግዚአብሔር እኔን ሊጠቀም መረጠ።

ጌታ ጸሎታችንን እንዲመልስልን እና ስለ ክርስቶስ እንድንናገር እድሎችን እንዲሰጠን መጠበቅ አለብን። ድፍረት እንዲሰጥህ ጸልይ። የማኅበራዊ ግንኙነት ሀብትህን ለመጠቀም ፈቃደኛ ሁን። እግዚአብሔር ባለህበት የሥራ ቦታ ያስቀመጠህ ለዓላማ ነው።

አሾክ ናቻኒ