በክርስትና ሕይወት ውስጥ ስላለው ቀጣይነት ያለው ቅድስና ያለኝን ጎዶሎ የሆነ ዕውቀት የተገነዘብኩበት ጊዜ እስካሁን ድረስ አዕምሮዬ ውስጥ ታትሞ ቀርቷል። ይህ አጋጣሚ በአንድ አነስተኛ ቡድን ውስጥ በእኛ የመቀደስ ሂደት ውስጥ የእኛ ድርጊት ድርሻና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በምንወያይበት ወቅት ነው። ውይይታችን እየተደረገ በነበረበት ጊዜ ሰዎች በቅድስና እንዲያድጉ ምን እንደረዳቸው፣ ብሎም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅድስና ለማደግ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደ ተማሩ እያካፈሉ ነበር፤ ልክ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ ጸሎት ወዘተ የመሳሰሉትን ነገሮች። ከዚህ በተጓዳኝ፣ ሰዎቹ በተደጋጋሚ መንፈስ ቅዱስ እነርሱን የመቀደስ ሥራውን እንደ ሠራ እየጠቀሱ ነበር። በስተመጨረሻ ግን አንዲት እውነተኛና ግልጽ የሆነች ሴት እንደመባረቅ ዐይነት ብላ፣ “እኔ አይገባኝም፤ እንዴት ነው በክርስትና ማደግ የሚቻለው?” ብላ የሆዷን አፈነዳችው።
ትንሽ የኋላ ታሪኩን ለመስጠት ይህች ሴት ለብዙ ዓመታት ኢየሱስን ተከትላለች፤ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ እድገቷ እንደቆመ ይሰማታል። መጽሐፍ ቅዱስን ታነባለች፤ ትጸልያለች፤ እንዲሁም በየእሁዱ ቤተ ክርስቲያን አትቀርም። ሆኖም ግን በውስጧ በሰዎች ላይ ቂምና መራርነት ይዛለች፤ እንዲሁም የምትጸጸትባቸውን ነገሮች ሰዎችን ተናግራለች። ኀጢአቷም እግዚአብሔርን እንዳሳዘነ ተረድታለች። ስለዚህም ተረጋግታ እግዚአብሔር እስኪቀድሳት መጠበቅ እንደማትችል ታውቀዋለች። በዚህ ላይ ደግሞ አሁን እየገባት ያለው ነገር እርሷ እያሳየችው ባለው ጥረት መጠን እድገቷ የዚያን ልክ ያለመሆኑን እውነታ ነው። በብዙ እየጣረች ነገር ግን የትም እየደረሰች አይደለም። በዚያው ማታ ቀደም ብሎ መንፈሳዊ ልምምዶቻችን ቀጥተኛ የዕድገታችን ምክንያቶች ካደረግናቸው እድገታችን አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ሐሳብ ሰጥቼ ነበር፤ ምክንያቱም ትኩረታችን ከክርስቶስ ወንጌል ይልቅ እኛ ላይ ስለሚሆን። በትክክል መናገር የምችለው የሰጠሁት ሐሳብ ምንም ቢያስፈራትም ከእርሷ ሕይወት ጋር ቀጥታ ተዛማጅነት ነበረው።
ይህም ሆኖ ጥያቄዋን መመለስ አልቻልኩም ነበር፤ ምክንያቱም ስለ ድነት የነበረኝ አመለካከት ቁርጥራጭ ነበር። ሙሉና ተፈጥሮዊ የሆነ የድነት አረዳድ ስለ ሌለኝ የድነት ሂደት አካል የሆኑት በእግዚአብሔር ፊት መጽደቅና ቀጣይነት ያለው የክርስትና ቅድስና እርስ በርስ ይጋጩብኝ ነበር። ሰዎች የመለስኩ እንዲመስላቸው ብቻ የተወሰነ እርስ በእርሱ የማይጣጣም ነገር ቀባጠርኩና ለዕረፍት እንዲወጡ አደረኩ። ሆኖም ግን የተፈጠረውን ግርታ ምንም ሊፈታው አልቻለም።
የመጋቢ ኀላፊነት
ሚስቴ ከሕፃን ሴት ልጃችን ጋር የእናትና ልጅ ሥነ ልቦናን ሳታብራራ እንደምትረዳ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም ቀጣይነት ስላለው የክርስትና ቅድስና እድገት ነገረ መለኮት የግድ ማብራራት አለበት ብዬ አላስብም። ክርስቶስን እየተመገብን በደንብ ማደግ እንችላለን ምንም እንኳ እንዴት ይህ ሂደት እንደ ተፈጸመ ማስረዳት ባንችልም። ከላይ ያለውን ምሳሌ ለመቀጠል፣ በእናትና ሴት ሕፃን ልጅ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ችግር ቢከሰትስ? በእርግጠኝነት መናገር የምችለው የሆነ ሰው ችግሩን የሚረዳና ሊያግዝ የሚችል ሰው ይኖራል።
ለዚህም ነው መጋቢያን የቅድስናን ነገረ መለኮት ማወቅ የሚጠበቅባቸው። “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አማካሪ ሥራ አይደለምን?” ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ፤ መልሱ ልክ ነው የሚል ነው። ሆኖም ግን መጋቢያን ማለትም በዋነኝነት በማስተማርና በስብከት የሚያገለግሉ ሕዝቦቻቸውን በትክክለኛው አቅጣጫ ለመምራት ቀጣይነት ያለውን ክርስቲያናዊ የቅድስና ነገረ መለኮትን የማስተማር ኀላፊነት አለባቸው። አስቡት እስኪ ለሕዝባችሁ ቅድስናን ታሳቢ በማድረግ ካልሰበካችሁ ምን እያደረጋችሁ ነው? በአዕምሮ ዕውቀት ብቻ ሕዝባችሁን ማሳደግ እንደማታሰቡ አስባለሁ ከዚያም ሲብስ ሰዎችን አዝናንቶ የመላክ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እሙን ነው። ሕዝባችሁ የሕይወት ለውጥ እንዲያመጡ ትፈልጋላችሁ። ነገር ግን ጥያቄው ይህ እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጣችኋል ወይ ነው? ይህ ካልሆነ ሕዝባችሁ በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄዱ እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ?
ምንድን ነው በተደጋጋሚ የምንስተው ነገር?
ቀጣይነት ያለው የክርስትና ቅድስና ላይ የተጋረጡት አደጋዎች አንዱ ቅጥ ያጣ ነፃነት ሲሆን ሌላው ደግሞ አጉል ወግ አጥባቂነት ነው። አጉል ወግ አጥባቂነት ቅድስናን እኛ እንደምንሠራው ሥራ ያየዋል። ምናልባት የተወሰኑ ሥራዎችን ብሠራ ድነቴን ማግኘት እችላለሁ ይላል። ወይም ደግሞ እነዚህን የማደርገው በእግዚአብሔር ዘንድ የተሻለ ሞገስ ለማግኘት ነው የሚል ሐሳብ አለው። “እነዚህን ነገሮች ባቆምና እንዚህን ነገሮች ብጀምር ጥሩ እሆናለሁ” ብሎም ያስባል። ይህ አጉል ወግ አጥባቂነት ነው ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ኅብረት የሚመነጭ መታዘዝ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖረን ለመታዘዝ መጣር ስለሆነ ነው።
ሁለተኛው ስሕተት ቅጥ ያጣ ነፃነት ነው፤ ይሄንን ደግሞ የሚቀበሉት ሕግ ጠሎች ይባላሉ። ይህ የተሳሳተ ሐሳብ የሚነሣው በክርስቶስ የተደረገልን ነገሮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እኛ መሥራት ላለብን ሥራ ምንም ክፍተት አይተውም። የሕግ ጠሎች ከፍተኛ ውድቀት የራሳቸው የተሳሳተ ተዛምዶና ጥረት መና ሲቀር የሚደርሱበት የተሳሳተ ድምዳሜ ጭራሹኑ ምንም ጥረት አለማድረግ የሚል ይሆናል።
እስቲ አሁን ደግሞ ለቅድስና ግልጽ አቅጣጫ ካልተቀመጠ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል እንመልከት። ሰዎችን አጉል ወግ አጥባቂነታቸውን ቅጥ ባጣ ነፃነት እንዲዋጉት፣ በተቃራኒው ደግሞ ቅጥ ያጣ ነፃነትን በወግ አጥባቂነት እንዲዋጉት ልናበረታታ እንችላለን። አስታውሳለሁ! ለቅድስና ያላቸውን ፍላጎት አደጋ ላይ እየጣልነው እንደሆነ ስለሚያስቡ የተወሰኑ የኮሌጅ ተማሪዎች ወንጌልን መስበክ እንዳቆም ሲነግሩኝ። አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች አሉ በግልጽ ቢያወሩት፣ ኀጢአትን በመሥራታቸው የሚጽናኑ፤ ምክንያቱም አጉል ወግ አጥባቂ አለመሆናቸውን ስለሚያረጋግጥላቸው። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ቅድስና አይደለም፤ እኛም ቢሆን ይህን ዐይነት አስተሳሰብ በፍጹም ማበረታታት የለብንም።
የውሸት ቅድስናን ማስተዋወቅ ከምታስቡት በላይ ቀላል ነው። ብዙ ሰባኪዎችን ሰምቻለሁ በሕዝባቸው ላይ ብዙ ማድረግ ያለባቸውን ነገር እየጫኑ ነገር ግን በምን ኀይል ያንን ማድረግ እንደሚችሉ ምንም የማይናገሩ። የጳውሎስ “ስለዚህ ጸጋ እንዲጨምር በኀጢአት ፀንተን እንቀጥል?” ለሚለው ጥያቄ አዎን የሚል መልስ የሚመልሱ የሚመስሉ፣ ብዙ ጸጋና የቅድስና ኑሮ ግንኙነት የሌላቸው ነገሮች የሚያስመስሉ ስብከቶችን ሰምቻለሁ። እነዚህ ስሕተቶች የሚስተካክሉት የሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማዕከል ክርስቶስን ባደረጉ ስብከቶች ነው። ነገር ግን ቀጣይነት ያለው የቅድስና ሕይወት ነገረ መለኮት ያስፈልገናል፤ ስለዚህም አንድ እርምጃ ወደ ፊት በመሄድ፣ “ክርስቶስ ጋር ስንደርስ እንዴት ነው ክርስቶስን መልበስ ምንችለው ብሎም ደግሞ እንዴት ነው ለሥጋ ምኞትስ ምንም ዕድል ፈንታ የማንሰጠው?” ብለን እንጠይቃለን።
አሁን እያልኩ ያለሁት እያንዳንዱ ስብከቶች ረጃጅም የቅድስና ሕይወት አስተምህሮን ማካተት አለባቸው አይደለም። በስብከታችን መካከል ክርስቶስ ጋር ስንደርስ በአንድ አረፍተ ነገር ሊገለጽ ይችላል። ምናልባት በዚህ ሐሳብ ለተረበሸ ወይም በራሱ የበቃ ለመሰለው ሰው የምትናገሩት ነገር ሁሉም ሰው የሚያውቀው ወይም ግልጽ ነገር ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ዋናው ነገር “ክርስቶስን መልበስ” እና “በላይ ያለውን ነገር ማሰብ” ከቅድስናችን ጋር በተያያዘ ዋነኛ ትዕዛዞች ከሆኑ፣ እነርሱን መታዘዝ ምን ማለት እንደሆኑ ማወቅ አለብን፤ ከዚያም ሲያልፍ በስብከታችን ውስጥ ግልጽ መሆን አለብን።
በክርስቶስ ውስጥ ያለው የቅድስና ኑሮ
ትክክለኛ የሆነ የቅድስና ነገረ መለኮት ጸጋን ሳያሳንስ በቅድስና የማደግን አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት መስጠት አለበት። በተቃራኒው በቅድስና የማደግን አስፈላጊነት ሳያሳንስ ጸጋ ላይ አጽንኦት መስጠት አለበት።
ይህን እንዴት ማድረግ እንችላለን? እዚህ ጋር አነስ ያለች ነገር ልተውላችሁ። የዚህ ጽሑፍ ትክክለኛ ግብ ስለ ቅድስና እንድታጠኑ ማድረግ ነው። የመጀመሪያው እርምጃ ቅድስናን ከድነት ጋር አያይዞ ማሳየት ነው። “ቅድስና” እና “መዳንን” እንደ ሁለት የተለያዩ እርስ በእርስ እንደሚወዳደሩ ነገሮች ማውራት ማቆም ይኖርብናል። (ኤፌሶን 2፥8-9) “ በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም” የሚለውን ጥቅስ፣ “ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን” (ኤፌሶን 2፥10) ከሚለው ለይቶ መጥቀስ ልናቆም ያስፈልጋል። ድነት ቀጣይነት ያለውን ቅድስናን ያካትታል፤ ነገር ግን እንደ ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን እንደ አንድ ክፍሉ አድርጎ ነው። አትኩሮት መስጠት ያለብን ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነፃ ጸጋና መልካም ሥራ መካከል ምንም ውጥረት የለም።
ለምንድን ነው የሌለው?
ይህ ጥያቄ ወደ ሁለተኛው ሰፊ ሐሳብ ይመራኛል። ይኸውም ድነት ማለት በክርስቶስ ውስጥ መሆን ማለት ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አብዛኛውን ጊዜ ድነትን ስናስብ ተጠቅልለው እንደ ተከመሩ ብዙ ስጦታዎች ነው። ስጦታዎቹን ስም ለመስጠት ያክል አንዱ ስጦታ “ይቅርታን ማግኘት” ሌላው “መንፈስ ቅዱስ” አንዱ ደግሞ “ቤዝዎት” ሊሆን ይችላል።
እውነታው ድነት ማለት እኛ ለድነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የሆነውን ክርስቶስን ለድነታችን መቀበል ነው። እኛ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ውስጥ ነን።” ምክንያቱም ሁሉም ስጦታ እርሱን በመቀበል የሚገኝ ስለሆነ በእርሱ በኩል ፍጹም የሆነ ቅንጅት አላቸው። የኀጢአት ይቅርታና የተቆጠረልንን ጽድቅ ቁጭ ብሎ ለማረፍ ሳይሆን ምንጠቀምበት ይልቁንም ወደ ክርስቶስ ተጠግተን ከእርሱ በሚገኝ እርዳታ የጽድቅን ሕይወት ለመኖር ነው። ደግሞም የጽድቅን ሕይወት ስንኖር በእግዚአብሔር ፊት መጽደቃችንን ችላ አንለውም፤ እንዲያውም በእግዚአብሔር ቅድስና በመመሰጥ በክርስቶስ ስላገኘነው የተቆጠረለንን ጽድቅ የጨመረ አድናቆት ይኖረናል። ይህም በእግዚአብሔር ፊት የመቆም መብታችን ነው። የክርስትና ሕይወታችንን የሚያያይዘው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው ፤ ይኸውም ክርስቶስን ለጽድቃችን ከሞት ያስነሣው መንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖረን ያደርጋል (ሮሜ 4፥25)፤ በፍሬ ይሞላናል ከዚያም በተጨማሪ እኛን ወክሎ በእግዚአብሔር ፊት ይጸልይልናል።
በሌላ አገላለጽ በድነታችን በኩል ያለው የትኛውም እድገት ያለ ጥርጥር ወደ ክርስቶስ ማንነት እና ከእርሱ ጋር ወዳለን መንፈሳዊ ኅብረት ጠልቀን እንድንገባ ያደርገናል፤ ይህም በእርሱ ካገኘነው በረከት ጋር ያገናኘናል። በክርስቶስ ሁሉም መንፈሳዊ በረከቶች የኛ ናቸው። ድነታችን እንደ አንድ ጥቅል ስናየው አንዱን ጥቅም (በረከት) ከሌላው ማበላለጥ አንችልም። ሲቀጥልም ወግ አጥባቂነትን ቅጥ ባጣ ነፃነት ለመዋጋት አንሞክርም። ወግ አጥባቂነትም ሆነ ቅጥ ያጣ ነፃነትን በክርስቶስ እንዋጋቸዋለን።
መቀደስን አጥኑ!
ሴትየዋ ስለ ጠየቀችው ጥያቄ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ቅድስናን እንዳጠና ስላነሣሣኝ። ምንም ያኽል ይህ እውነት ቢገባንም ሁሌም ያልተረዳነው ነገር አለ፤ ከዚያም በላይ ከቁጥር በላይ የሆነ በሕይወታችን ልንለማመዳቸው የተገቡ ነገሮችም አሉ። መሠረታዊው የቅድስና አቅጣጫ እንኳ ካለን እርሱም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነ የምንመራቸውን ሰዎች ወደ ክርስቶስ ጠልቀው እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፤ ይህም ወደ ጽድቅ ሕይወት ዘልቀው ይገባሉ ማለት ነው።
በወንጌላውያን መካከል በእግዚአብሔር ፊት የመቆም ጽድቅን (መጽደቅን) እንድንረዳ ከፍተኛ ግፊት አለ፤ ይህ ጥሩ ሆኖ ሳለ በክርስትና ቀጣይነት ያለውን መቀደሳችንን ችላ በማለት ግን መሆን የለበትም።
በማይክ ክራይስት