ብዙ ጊዜ “ቅዱሳት መጻሕፍት በገላጭ ስብከት እንዴት ይተገበራሉ?” የሚል ጥያቄ እሰማለሁ። ከዚህ ጥያቄ ጀርባ ብዙ መነሻ ሐሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ጠያቂው ይህን የሚለው፣ የሰማውን (ወይም የሰበከውን) “ገላጭ” ስብከት ነገር ግን በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ውስጥ በሚገባ ከተዋቀረ ሌክቸር ምንም ልዩነት የሌለው ንግግር፣ መጋቢያዊ ጥበብ እና የመልእክቱ አንገብጋቢነት የማያሳይን ስብከት እያስታወሰ ሊሆን ይችላል። እነዚህ የሰማቸው ገላጭ ስብከቶች ጥቂት ተግባራዊ ሐሳብ ስለኖራቸው ወይም ጠያቂው የስብከቱን ተግባራዊ ሐሳብ እንዴት መለየት እንዳለበት ላያውቅ ይችላል።
በካምብሪጅ የኖረው ታላቁ የዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የፒዩሪታን የሥነ መለኮት ምሁር ዊልያም ፐርኪንስ ሰባኪዎች ለስብከታቸው የተለያዩ ዐይነት ሰሚዎችን ታሳቢ እንዲያደርጉ ይናገራል። ደግሞም ለእያንዳንዳቸውም ማለትም ለልበ ደንዳና ኀጢአተኞች ፣ ለተጠራጣሪዎችና ጠያቂዎች ፣ የደከሙ ቅዱሳን ፣ ወጣት ተስፈኞች ፣ ወዘተ… ተግባራዊ ሐሳብን እንዲያዘጋጁ ይመክራል።
የፐርኪንስ ምክር በጣም ጠቃሚ ነው፤ እንደዚህም እያደረግን እንዳለ ተስፋ አደርጋለሁ። የተዛምዶውን ርዕሰ ጉዳይ በመጠኑም ቢሆን በተለየ መንገድ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ይኸውም የተለያዩ ዐይነት ሰሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ዐይነት ተዛምዶዎችና ተግባራዊ ሐሳቦች አሉ። የእግዚአብሔርን ቃል ምንባብ ወስደን በግልጽ፣ በአሳማኝ፣ በአንገብጋቢ ሁኔታ ስናብራራ በክርስቲያናዊ ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙ ሦስት የተለያዩ ችግሮችን የሚያንጸባርቁ ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ተዛምዶዎች አሉ። አንደኛ፣ የምንታገለው ካለማወቅ ጋር ነው። ሁለተኛ፣ መጀመሪያ ከገመትነው በላይ ብዙ ጊዜ ከጥርጣሬ ጋር እንታገላለን። ሦስተኛ፣ በቀጥታ ከኀጢአት ጋር እንታገላለን። ይህም እያወቁ ካለመታዘዝ ጋር ወይም ስለ ኀጢአት ያለ ቸልተኝነት ጋር ሊሆን ይችላል። ሰባኪ እንደ መሆናችን መጠን የእግዚአብሔርን ቃል በምንሰብክበት ጊዜ ሁሉ በራሳችንም ሆነ በአድማጮቻችን ላይ በሦስቱም መንገዶች ለውጦችን ለማየት እንፈልጋለን። ሦስቱም ችግሮች የተለያዩ ትክክለኛ ተዛምዶዎችን ይፈልጋሉ።
አለማወቅ
በወደቀው ዓለም ውስጥ ዕውቀት ማጣት መሠረታዊ ችግር ነው። እግዚአብሔርን ከእኛ ዓለም አርቀነዋል። ከፈጣሪያችን ጋር የነበረን ቀጥተኛ ኅብረትን አጥተነዋል። እንግዲያው ለሰዎች ስለ እግዚአብሔር እውነቱን ማሳወቅ በራሱ ሁነኛ የተዛምዶ ዐይነት ሲሆን እኛ በጣም የሚያስፈልገን ይህ መሆኑ ምንም አያስደንቅም።
ይህ ለቀዝቃዛ ወይም ስሜት አልባ ስብከት ማስተባበያ ለመስጠት አይደለም። የሆነልንን በሚናገሩ ስብከቶች እንደሆነው ሁሉ ለማስጠንቀቂያ መልእክቶችም በሙሉ እውነተኛ ስሜት ማገልገል እችላለሁ። የወንጌል ትእዛዛት ማለትም ንስሓ መግባት እና ማመን ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ እኛ እና ስለ ክርስቶስ የሆነልንን ከሚናገሩ መግለጫዎች ውጪ ልንረዳቸው አንችልም። መረጃ ወሳኝ ነው። የተጠራነው እውነትን እንድናስተምር እና ስለ እግዚአብሔር ታላቅ መልእክት እንድናውጅ ነው። መልእክቶቻችንን የሚሰሙ ሰዎች ከአለማወቅ ወደ እውነተኛ ዕውቀት እንዲሸጋገሩ እንፈልጋለን። እንዲህ ዐይነቱ ከልብ የሆነ የማስተማር ይዘት በራሱ አንዱ ተዛምዶ ነው።
ጥርጣሬ
ጥርጣሬ ከቸልተኝነት የተለየ ነው። በጥርጣሬ ጊዜ የምናውቃቸውን ሐሳቦች ወይም እውነቶች መልሰን እንጠይቃለን።
ይህ ዐይነቱ ጥያቄ በክርስቲያኖች ዘንድ ብርቅ አይደለም። በርግጥ፣ በስብከታችን ውስጥ በአስተሳሰብ ሊመረመሩ እና ሊሞገቱ ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ጥርጣሬ ሊሆን ይገባል። ጥርጣሬን መፍታት ሰባኪ ከማያምኑት ጋር ብቻ የሚያደርገውን የእቅበተ እምነት ሥራ አይደለም። በየሳምንቱ ስብከቶችን ለማዳመጥ የሚቀመጡ አንዳንድ ሰዎች ሰባኪው ስለ ክርስቶስ ወይም እግዚአብሔር ወይም አናሲሞስ የጠቀሰውን ሁሉንም እውነታ በሚገባ ያውቁ ይሆናል፤ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች እውነት መሆን አለመሆናቸውን ለማመን ይቸገራሉ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጥርጣሬያቸውን ሊገልጹት ይቅርና ጥርጣሬ እንዳላቸው ላይታወቃቸው ይችላል።
ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት መመርመር ስንጀምር፣ ጥያቄዎች፣ ርግጠኛ ያልሆኑ ነገሮች እና ማመንታት፣ እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ የጥርጣሬ ግፊቶች ከታማኝነት ጉዞ ሊያርቁን እንደሚችሉ እንድናውቅ ያደርጉናል። ለእንደዚህ ዐይነት ሰዎች ምናልባት ለእንደዚህ ዐይነት የልባችን ውቅር፣ የእግዚአብሔርን ቃል እውነትነት እና የማመንን አንገብጋቢነት ልንሞግት እና ልናሳስብ እንወዳለን። የተጠራነው የእግዚአብሔርን ቃል እውነትነት ለሰሚዎች ልናበስር ነው። መልእክቶቻችንን የሚሰሙ ሰዎች ከጥርጣሬ ወጥተው በሙሉ ልብ በእውነት እንዲያምኑ እንፈልጋለን። እንዲህ ዐይነቱ ሞጋች ፣ ስለ እውነት እንድናስብ የሚያደርጉ ስብከቶች ሌላ ዐይነት ተዛምዶዎች ናቸው።
ኀጢአት
ኀጢአት በዚህ በወደቀው ዓለም ውስጥ ሌላኛው ችግር ነው። አለማወቅ እና ጥርጣሬ በራሳቸው ኀጢአቶች ወይንም የኀጢአት ፍሬዎች ሊሆኑ ወይንም ደግሞ ሁለቱንም አማራጭ ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ኀጢአት በርግጠኝነት ካለማወቅ ወይም ከጥርጣሬ በላይ ነው።
ስብከትህን የሚሰሙ ሰዎች ባሳለፉት ሳምንት ውስጥ እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ጋር እንደታገሉ እና ቀጣይ ሳምንትም እርሱን ከመታዘዝ ጋር እንደሚታገሉ ርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ኀጢአቶቹ የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶቹ ድርጊትን በመፈጸም አለመታዘዝ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ መደረግ ያለበትን ባለማድረግ አለመታዘዝ ይሆናሉ። ነገር ግን የማድረግም ሆነ ያለማድረግ ኀጢአት ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ነው።
የእግዚአብሔርን ሕዝብ በቅድስና እንዲኖር እና የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያንጸባርቅ ሕይወት እንዲፈልግ መጠየቅ የስብከት አካል ነው። ሰሚዎቻችን ከኀጢአተኛ አለመታዘዝ በደስታ ወደ መታዘዝ እንዲመጡ እና በቃሉ እንደ ተገለጸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲታዘዙ እንፈልጋለን። እንዲህ ዐይነቱ ለጽድቅ ያለ ምክር በርግጥም ተዛምዶ ነው።
ወንጌል
በምንሰብክበት ጊዜ ሁሉ ማዛመድ ያለብን ዋናው መልእክት ወንጌል ነው። አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሥራች ገና አያውቁም። አንዳንዶቹ ደግሞ ስብከታችሁን እየሰሙ ሐሳባቸው ተበታትኖ፣ በቀን ቅዠት ውስጥ ሆነው ወይንም ሐሳባቸው በሌላ ነገር ተወስዶ ይሆናል። ስለዚህ ስለ ወንጌል ሁሌም ልንናገር ይገባል።
ሌሎች ደግሞ ሰምተው፣ ተረድተውት እና ምናልባትም እውነቱን ተቀብለው ሊሆን ይችላል፣ አሁን ግን በመልእክትህ ውስጥ የምትናገረውን ጉዳዮች በመጠራጠር እየታገሉ ይሆናል። እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን ምሥራች እውነት በማመን እንዲጸኑ ማስታወቅ ያስፈልጋል።
አንዳንድ ሰዎች ወንጌል ሰምተው እና ተረድተው ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ለኀጢአታቸው ንስሓ ለመግባት የዘገዩ ይሆናሉ። ምናልባት የወንጌልን መልእክት እውነት ሊቀበሉ ቢወዱም ኀጢአታቸውን መተው እና በክርስቶስ መታመን አይፈልጉም ይሆናል። ለእንደዚህ ዐይነት ሰሚዎች፣ አንተ ማዘጋጀት የምትችለው በጣም ኀይለኛ ተዛምዶ ኀጢአታቸውን እንዲጠሉ እና ወደ ክርስቶስ እንዲሸሹ መምከር ነው። በስብከታችን ሁሉ፣ ወንጌልን በማሳወቅ በማበረታታትና በመምከር ተግባራዊ ለማድረግ መጣር አለብን።
እኛ ሰባኪዎች የእግዚአብሔርን ቃል በስብከታችን ላይ በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ከሚያጋጥሙን አንዱ የተለመደ ፈታኝ ሁኔታ በአንድ የተለየ መልኩ ችግር ያጋጠማቸው ግለሰቦች ሰባኪው ለነሱ የሚሆን ተዛምዶ አላዘጋጀልንም በሚሉበት ወቅት ነው። ትክክል ናቸው? የግድ ትክክልም ላይሆን ይችላል። እያንዳንዱን የተዛምዶ ክፍል ደጋግመህ መናገር ስትጀምር የስብከቱ ውጤትህ ሊሻሻል ቢችልም እንኳ ኀጢአትን እንዲተዉ መምከርን መስበክ ስሕተት አይሆንም።
አንድ የመጨረሻ ማስታወሻ። ምሳሌ 23፥12 “ልባችሁን ወደ ተግሣጽ ጆሮቻችሁንም ለዕውቀት ቃል አድርጉ” ይላል። በእንግሊዘኛ ትርጉሞች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተግባራዊ አድርጉ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሁልጊዜ ማለት ይቻላል (ምናልባት ሁልጊዜ?) የሰባኪውን ሥራ (ሥነ ስብከት እንደሚያስተምረን) ወይም የመንፈስ ቅዱስን ሥራ (ስልታዊ ሥነ መለኮት እንደሚያስተምረን) ሳይሆን ቃሉን በሚሰማ ሰው የሚተገበረውን ሥራ የሚያመለክት ይመስላል። እኛ የተጠራነው ቃሉን ለልባችን እንድንተገብር እና ራሳችንን ለዚህ ሥራ እንድናውል ነው።
ይህ ምናልባት በሚቀጥለው እሁድ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ጥቅም ልናደርገው የምንችለው ዋነኛው ተዛምዶ ነው።
በ ማርክ ዴቨር