አገልግሎት ከሕይወት ይበልጣል | ሐምሌ 13

ይሁን እንጂ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።” (ሐዋርያት ሥራ 20፥24)

በአዲስ ኪዳን መሠረት “አገልግሎት” ሁሉም ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት ነገር ነው። በኤፌሶን 4፥11-12 ላይ እንደምንመለከተው፣ ቅዱሳን ለአገልግሎት እንዲበቁ መጋቢዎች የማነጽ ኀላፊነት አለባቸው። ነገር ግን አገልግሎቱን የሚያገለግሉት ሁሉም ክርስቲያኖች ናቸው።

ክርስቲያኖች ሁሉ እንደሚለያዩት፣ አገልግሎትም እንደዚሁ ልዩ ልዩ ነው። አገልግሎት እንደ ሽምግልናና ድቁና ያለ የአገልግሎት ቢሮ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በሁሉ ክርስቶስን ለመምሰል እና የሌሎችን ፍላጎት ለማሟላት የተዘጋጀ የአኗኗር ዘይቤ ነው።

 “ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” እንደሚለው ማለት ነው (ገላትያ 6፥10)። አገልግሎት ማለት፣ ሐኪምም እንሁን አናጢ፣ ሌሎች ሰዎችን በእምነትና በቅድስና ለእግዚአብሔር ክብር እንዲያድጉ መሥራት ነው።

አገልግሎታችሁን መፈጸም በሕይወት ከመቆየት በላይ አስፈላጊ ነው። ይህ እውነት፣ ለአገልግሎት የተሰጡ ሰዎችን ሕይወት እንድንመለከት ያበረታታናል። ልክ ጳውሎስ በሐዋሪያት ሥራ 20፥24 ላይ፣ “ይሁን እንጂ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት” ብሎ ስለ አገልግሎቱ በተናገረበት መንገድ አብዛኛዎቹ ተናግረዋል። እግዚአብሔር የሰጠንን አገልግሎት መፈጸም ከሕይወት የበለጠ አስፈላጊ ነው።

ምናልባት ለማገልገል ሕይወታችንን ማትረፍ ይኖርብናል ብለን ልናስብ እንችል ይሆናል። በተቃራኒው ሕይወታችንን የምናጣበት መንገድ የአገልግሎታችን ትልቅ ግብ ሊሆን ይችላል። ዕድሜው ገና በሠላሳዎቹ ብቻ ለነበረው ለክርስቶስም ይህ እውነት ነበር።

አገልግሎታችንን ለማጠናቀቅ ብለን ራሳችንን በሕይወት ለማቆየት መጨነቅ አይኖርብንም። ለአገልግሎታችን የተወሰነውን ጊዜ እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል። ሞታችን የአገልግሎታችን መቋረጥ ሳይሆን የአገልግሎታችን የመጨረሻ ተግባር የሚሆንበትን ጊዜ እርሱ ራሱ ይወስናል።

ስለዚህም ሄነሪ ማርቲን፣ “ለእግዚአብሔር የምሠራው ሥራ ካለኝ ልሞት አልችልም” ማለቱ ልክ ነው ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ ሥራዬን እስክጨርስ ድረስ የማልሞት ነኝ ማለት ነው። ስለዚህ አገልግሎት ከሕይወት የበለጠ እጅግ አስፈላጊ ነው።