ኢየሱስ የእግዚአብሔር አሜን ነው | መጋቢት 13

በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው። (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)

ጸሎት የቀድሞው እና የወደ ፊቱ ሕይወታችን የሚያያዝበት ቦታ ነው። ይህን የምለው ጳውሎስ በአስገራሚ ሁኔታ ጸሎትን ከእግዚአብሔር አዎንታ ጋር እንዳያያዘው ለማሳየት ነው።

2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20 ላይ እንዲህ ይላል፦ “እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ ‘አሜን’ የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።“ ይህንን ለማብራራት እንሞክር።

ለማለት የፈለገው ይህንን ነው፦ “እኛም በክርስቶስ አማካይነት በጸሎታችን ለእግዚአብሔር አሜን የምንለው፣ ወደ ፊት ለምንጠባበቀው በረከት እና ጸጋ እግዚአብሔር ክብሩን እንዲያገኝ ነው።“

ክርስቲያኖች ጸልየው ሲጨርሱ አሜን ለምን እንደሚሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ መልሱ ይህ ነው፦ “አሜን“ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ እና ሌሎችም ቋንቋዎች በቀጥታ ሳይተረጎም የተወሰደ ቃል ነው።

በዕብራይስጥ ጠንካራ ስምምነት ማለት ነው (ዘኁልቍ 5፥22ነህምያ 5፥138፥6)። “እስማማለሁ“ ወይም “የተባለውን እቀበላለሁ“ ወይም ደግሞ “እውነት ነው“ ማለት ነው። በአጭሩ “አሜን” ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ስንነጋገር ከልብ የሆነ “አዎን“ ማለት ነው።

አሁን በ2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20 ሁለቱ ክፍሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ተመልከቱ፦ የመጀመሪያው ክፍል “በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ ‘አዎን’ የሚሆኑት በእርሱ ነውና“ ሲል፣ ሁለተኛው ደግሞ “እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ ‘አሜን’ የምንለው በዚህ ምክንያት ነው“ ይላል።

“አሜን” እና “አዎ” አንድ ትርጉም እንዳላቸው ስንረዳ ዐረፍተ ነገሩ እንዲህ ይላል፦ በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በገባልን የተስፋ ቃሎች ላይ ‘አዎን’ ሲለን፣ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ስንጸልይ ‘አሜን’ እንለዋለን።