ወደ ድንቅ የእግዚአብሔር ምስጢር ተራሮች ገስግሱ

የእግዚአብሔርን አሠራርና መንገድ አለማወቃችንን እርሱን ለማድነቅና ለማምለክ እንደ መሠረት የሚያገለግል መሆኑን የሚናገሩ የተለያዩ ጽሑፎችን አንብቤአለሁ። እንዲሁም የተለያዩ ሰባኪዎች በየምስባካቸው በዚህ መንገድ ሲሰብኩ ሰምቻለሁ። ይህንንም ለማድረግ የሚጠቀሙት ቃል “ምስጢር ” የሚለውን አዎንታዊ ቃል ሲሆን በዚህም የእግዚአብሔርን ክቡርነትና ልዕልና ምን ያህል እንደማናውቅ ተረድተን መደነቅ እንዳለብን ይነግሩናል።

ይህ አካሄድ ግን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚጠቁም ይመስለኛል። እንደዚህ በሚያደርጉ ሰዎችም አልሳብም። የጳውሎስ አካሄድ ከዚህ እጅግ የተለየ ነው። ጳውሎስ የሚለን እግዚአብሔር ይበልጥ የሚከብረው ምን ያህል እርሱን አለማወቃችንን በመረዳት ሳይሆን እርሱን ባወቅነው መሠረት ስንገረም፣ ስናመልከው፣ በደስታም ስንገዛለት ነው።

ስለ ተራራ ከፍታ ያለን አድናቆት ከተራራው ሥር ሆነን የተራራው ጫፍ ከፍ ብሎ በደመናው ሲከበብ ባለን ዕይታ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ወደ ተራራው ጫፍ የዓመታት ጉዞ አድርገን ስንደርስ ሰንሰለታማ የሆኑ ሌሎች ከዚያም ከፍ ያሉ ተራራዎች አይተን ልንደነቅ እንችላለን።

ከተራራው ሥር ሆነን ከደመናው በላይ ስላለው ነገር ጸሑፍ መጻፍ፣ ግጥሞችን መግጠም ለእግዚአብሔር የላቀ ክብር መስጠት አንችልም። ይልቁንም እግዚአብሔር እጃችንን ከጳውሎስ እጅ ወይም ከሌሎች የእስትንፋሰ መለኮት ጸሐፊዎችን እጅ እንዲያሲዘን ፈቅደን፣ ከፍ ወዳሉ የእግዚአብሔር እውነት መገለጦች ዕድሜ ልካችንን ብንገሰግስ ይሻላል።

“የማይመረመር እና የማይታወቅ“?

ከጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ በብዛት በተሳሳተ መንገድ የሚተረጎመውና አግባብ ባልሆነ መንገድ የሚጠቀሰው ጥቅስ የሮሜ ምዕራፍ 11 የመጨረሻ ክፍል ነው።

“የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም “የጌታን ልብ ያወቀ ማነው? አማካሪውስ የነበረ ማነው?” “እግዚአብሔር እንዲሰጠው፣ ለእግዚአብሔር ያበደረ ማነው?” ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን”(ሮሜ 11፥33-36)።

የዚህ ምንባብ ዋና ምልከታ ይህ ነው፦ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ባለጠግነት ያለውን መደነቅ ያሰፈረው በመገለጥ ቦታ ተክቶ ሳይሆን፣ በዐሥራ አንዱ ምዕራፎች በገለጻቸው እጅግ የሚያስደነቁ የእውነት መገለጦች ላይ በመመሥረት ነው። ገና ስላልተገለጠው ነገር ሳይሆን ስለተገለጠው ነገር ሲገረም እንመለከተዋለን። ይህ ጥቅስ የሚገኘው ጳውሎስ እጅግ ጥልቅ እና ሰፊ፣ ልንገምተውም ከምንችለው በላይ የሆኑ የእግዚአብሔርን አሠራሮች ካሳየን በኋላ ነው።

ከዚህ ክፍል ከፍ ብለን ያሉትን ሦስት ቁጥሮች ብናነብ ስለ እግዚአብሔር ልዩ አሠራር ይነግሩናል። በማይታወቅ ደመና የተሸፈኑ ሳይሆን ባልተጠበቀ፣ እጅግ በሚያስደንቅ እና እግዚአብሔርን ከፍ በሚያደርግ መንገድ የተገለጡ ናቸው። ጳውሎስ እግዚአብሔር ለአይሁድ እና ለአሕዛብ ያለውን ሐሳብ እንዲህ ሲል ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል፦

“እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ እንደነበራችሁ፣ ከእነርሱ አለመታዘዝ የተነሣ አሁን ምሕረት እንዳገኛችሁ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ለእናንተ ምሕረት ከማድረጉ የተነሣ፣ እነርሱም ምሕረት ያገኙ ዘንድ አሁን የማይታዘዙ ልጆች ሆነዋል፤ እግዚአብሔር ለሁሉም ምሕረት ያደርግ ዘንድ ሰውን ሁሉ ባለመታዘዝ ዘግቶታልና” (ሮሜ 11፥30-32)።

አምስት ደቂቃ ወስዳችሁ ይህንን አሰላስሉ። እጅግ የሚያስገርም እና እጅ በአፍ የሚያስጭን ነው። እንዲህ የተገረማችሁት ባለማወቅ ጨለማ ስለ ተከበባችሁ ሳይሆን በዕውቀት ብርሃን የምታዩትን ማመን ስለ ከበዳችሁ ነው።

“የማይመረመር” ግን ወደ ብርሃን የመጣ

በሌላ ክፍል ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንገድ “የማይመረመር”  በማለት ይገልጸዋል። ይህ ማለት ግን ከዕውቀት ውጪ የሆነ ማለት አይደለም።

“ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ። እንዲሁም ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ” (ኤፌሶን 3፥8-9)።

ይህ ክፍል፣ “ይቅርታ ወገኖች ሆይ፣ የክርስቶስ ባለጠግነት በምስጢር ጨለማ ውስጥ አለ፤ ስለዚህም ሊገለጥ አይችልም” እያለ አይደለም። ይልቁንም በተገላቢጦሽ፣ “እግዚአብሔር የጠራኝ እንዲሁም ጸጋ የሰጠኝ የተሰወረውን ምስጢር ወደ ብርሃን እንዳመጣ ነው! ስለ ክርስቶስ እየጻፍኩ ያለሁት ስለማይመረመረው የክርስቶስ ባለጠግነት ነው” እያለ ነው።

የማይመረመር ስንል በሦስት መንገዶች መግለጽ እንችላለን፦ (1) “በእግዚአብሔር ውስጥ ለዘመናት ተደብቀው ” የነበሩ ናቸው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን አይደሉም። (2) በሰው ልጆች ጥበብ ሳይሆን በመለኮታዊ መገለጥ ብቻ ሊታወቁ የሚችሉ ነገሮችን ነው። ጳውሎስ የጻፈልን ይህን መገለጥ ነው። (3) ወደ ተገለጠው እውነት በገሰገስን ቁጥር ይበልጥ ብዙ የምናየው እና የምንረዳው እውነት እንዳለ ለማመልከት ጭምር ነው። 

መታወቅ በላይ የሆነውን ለማወቅ

ይህ የመጨረሻው ነጥብ በሚቀጥለው የኤፌሶን መጽሐፍ ምዕራፍ ላይ በጳውሎስ ጸሎት ተረጋግጧል። እንዲህ ሲል ጳውሎስ ይጸልያል፦

“የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን እንደታገኙ ነው። እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅም በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው” (ኤፌሶን 3፥18-19)።

ይህ ነው! በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቶች አማካይነት እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ያሳየውን ልዩ መገለጥ ለመረዳት ችለናል። ይህም፣ “ከመታወቅም በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።” ወደ እግዚአብሔር ድንቆች ይበልጥ በገሰገስን ቁጥር ሊታወቅ የማይችለውን እያወቅን እንዲሁም ተራሮቹ ይበልጥ ከፍ እያሉ እንደሚሄዱ እየተረዳን እንመጣለን።

አስተማማኝ መሪ

ጳውሎስ በመገለጥ ተራራ እግር ሥር ሆኖ ከተራራው ጫፍ ካለው ደመና በላይ ስላለው ስለ “ማይመረመረው” ነገር ማውራት ከሚያረካቸው ሰዎች መካከል አልነበረም። ጳውሎስ የተጠራው፣ “የማይመረመረውን የክርስቶስ ባለጠግነት” እንዲሰብክ እንጂ ይህንን እውነት እንዲደብቅ አይደለም።

ጳውሎስ እግዚአብሔር የሚከብረው በማይመረመረው የምስጢር ሸለቆ ውስጥ ሆነን የተደበቀን ነገር ስናወድስ እንዳልሆነ ገብቶታል። እግዚአብሔር የሚከብረው ወደ እግዚአብሔር መገለጥ ተራራ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት አስተማማኝ መሪነት ተደግፈን የጉዞውን ግብዣ ስንቀበል ነው።

በጆን ፓይፐር