ታዳጊዎች ስማርት ስልክ ሊኖሯቸው ያስፈልጋል ወይስ?

ዕድሜያቸው ሃያ ቤቶች ውስጥ የነበሩና በአዳዲስ እና በሚያማልሉ የአይፖድ ቀጥሎም የአይፎንና አይፓድ ውጤቶች ዓለምን ያስደመሙ የሲልከን ቫሊ አብዛኞቹ ወጣቶች፣ በወቅቱ ልጆች አልነበሯቸውም። አንዳንዶቹ ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ቤት ውስጥ ያሉ ልጆች ነበሯቸው። አሁን ላይ አብዛኞቹ ልጆች አሏቸው። ብዙዎች ደግሞ ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ አካባቢ የሆኑ ልጆችን አድርሰዋል። እነዚህም ልጆች ወላጆቻቸው ከዓመታት በፊት በፈጠሯቸው ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሱሰኞች የሆኑ ናቸው።

ይህ የቶኒ ፋዴል ታሪክ ነው። ፋዴል፣ አፕል ኩባንያ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነበር። በቅጽል ስሙ የአይፖድ አያት በመባል ይታወቃል። እንዲሁም የአይፎን ስልክ በጥንስስ ደረጃ ላይ እያለ በንድፍ ቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው። የአይፎን ስልክን ዐሥረኛ ዓመት ክብረ በዓል ተከትሎ በሰጠው ቃለ ምልልስ እንዲህ ሲል ቃሉን ሰጥቷል፦ “ወደዚህች ዓለም ምንድን ነው ያመጣነው እያልኩ በማሰብ ብዙ ጊዜ ከእንቅልፌ ላብ አጥምቆኝ እነሣለሁ።”

ፋዴል ሦስት ልጆች ያሉት ሲሆን፣ ሊወገድ የማይችለውን የአይፎን ስልክ ሱስ የማስያዝ አቅም ለመመልከት በቅቷል። “ከልጆቼ ቴክኖሎጂዎችን ስነጥቃቸው ምን እንደሚከሰት አውቃለሁ። ከሰውነታቸው ላይ የሆነ ነገር ቆርሰህ እንደምትወስድባቸው ነው የሚሰማቸው። ስለ ነገሩ በጣም ስሜታዊ ይሆናሉ። ከቴክኖሎጂ በመለየት የሚመጣ መጎርበጥ፣ ሁለትና ሦስት ቀናት ያስቸግራቸዋል።

“ይህ በራሱ የተጠመደ ባህል፣ ክፉኛ መከርፋት ጀምሯል” ይላል ፋዴል። “ወላጆች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም ነበር። ሊያስተምሩ ይገባቸው የነበረው ነገር ይህ ነበር። ምክንያቱም ለራሳችንም አላወቅንም ነበር። ሁላችንም በእርሱ ተውጠናል።”

እውነት ነው። ሁላችንም ተውጠናል። በቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ያሉት፣ እንዲሁም ልጆች እና ወላጆች ሁላችንም ተውጠናል። አሁን ላይ እንዴት አድርገን ጥበብ በተሞላው መልኩ መጠቀም እንደምንችል ለመረዳት እየጣርን ነው።

 ታዳጊዎች፣ ስማርት ስልኮች እና ድባቴ

በዲጂታል ቴክኖሎጂ መዋጥ በፍጥነት ከሚለዋወጠው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሕይወት ጋር አብሮ ገጥሟል። በአንድ ወቅት ትዊን ሲቲ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (በውስጡ ከ 2,000 በላይ ተማሪዎችን የያዘ ነው) ውስጥ የምትሠራን ረዳት ርዕሰ መምህር ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ሥራዋ እንዴት እንደተቀየረ ጠየቅኋት።

“ብዙው ነገር እንዳለ ነው” አለች። “ነገር ግን ከ20 ዓመታት በላይ ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች ጋር ስሠራ፣ በከፍተኛ ደረጃ ከተለወጡ ነገሮች ውስጥ አንዱ፣ በፍጥነት የሚገኝ እርካታ እና ከሌሎች በሚያገኙአቸው አስተያየት ላይ ያላቸው ጥገኝነት ነው። ስንት ላይክ አገኘሁ? ስንት ፎሎወሮች ኖሩኝ? እንዲሁም አንዳንድ ነገሮችን በመለጠፍ ምን ያህል ላይክ መሰብሰብ እንደሚችሉ የማየት ጠንካራ ፍላጎት አለ። ይህም አልበቃ ብሎ ሰው ስለ እኔ ምን ይላል? ብለው ያስባሉ።”

“በዚህ ባሕርይ እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከምናያቸው የአእምሮ ጤና እክሎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለ” ትላለች። “ባለፉት ሦስት እና አምስት ዓመታት ሥራዬ እጅጉን ተቀይሯል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ደግሞ ከመጠን በላይ ከአእምሮ ጤና ጋር ከተያያዘ ነገር ጋር ስለምንጋፈጥ ነው። ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ምክንያት እንደሆነ ባላስብም፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ግን ዋና ድርሻውን እንደሚወስድ አስባለሁ። ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ካላቸው ግንኙነት አንሥቶ ራሳቸውን እስከሚመለከቱበት ዕይታ ድረስ፣ ሁሉንም ነገር ይቀይራል።”

ትውልድን ማውደም?

የፋዴልን የጭንቅ ላብ፣ እንዲሁም የዚህችን ረዳት ርዕሰ መምህር የዐይን ምስክርነት በጥሩ ሁኔታ ሊገልጽ የሚችል “ስማርት ስልኮች ትውልድን አውድመዋል ወይ?” የሚል ጠንካራ ርዕስ የተሰጠው አንድ ጽሑፍ ዘ አትላንቲክ በተባለ መጽሔት ላይ በቅርቡ ታትሞ ነበር።

በግርድፉ ዕድሜያቸው ከ 12 እስከ 22 የሚደርሱ እ.ኤ.አ ከ1995 እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ የተወለዱ ልጆች iGen የሚባል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ ይስተዋላሉ። “በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጆች ድባቴ እና ራስን የማጥፋት መጠን እ.ኤ.አ ከ2011 ወዲህ ከመጠን በላይ ጨምሯል” ሲል ዢን ትዌንግ የተባለ ሌላ ጸሐፊ፣ iGen የተሰኘው ትውልድ እየገጠመው ስላለው ትግል ይጽፋል። ቀጥሎም፣ “የiGen ትውልድ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የአእምሮ ጤና ቀውስ በማስተናገድ ጫፍ ላይ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለዚህም ቀውስ ደግሞ ስልካቸው ጉልህ ድርሻ ይወስዳል” በማለት ጽፏል።

“በስልካቸው ስክሪን ላይ ብዙ ጊዜ ባጠፉ ቁጥር፣ የድብታ ምልክቶች የመታየት ዕድላቸው ይጨምራል።” እንዲሁም “ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ዘንድ በሚገኙ ሴቶች፣ እየጨመረ የመጣውን የድባቴ ምልክቶችን በመሸከም ዋነኛ ተጠቂዎች ናቸው።” ድባቴ  በወንድ እና ሴት ልጆች ዘንድ እየጨመረ እንደመጣ ትዌንግ ምንጮች አጣቅሶ ይናገራል። ከ2012-2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ የድባቴ ምልክቶች በወንድ ልጆች ዘንድ 21 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት በሴቶች ዘንድ የታየው የድባቴ ምልክት በ50 ከመቶ ከፍ ብሏል። ራስን ማጥፋትም እንዲሁ በሁለቱም ጾታዎች ዘንድ ጨምሯል። በወንዶች ዘንድ ሁለት እጥፍ የጨመረ ሲሆን በሴቶች ዘንድ ሦስት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል።

እያየነው ስላለው የድባቴ መጨመር ከማውቀው ተነሥቼ እንዲሁም ስለ ስልኮቻችን አማላይነት ከተረዳሁት በመነሣት እየተጋፈጥን ያለነው የሕይወት ምንነት እና ከሌሎች ተቀባይነት የማግኘት የሕልውና ጥያቄዎች ናቸው እላለሁ። እነዚህ ጥያቄዎች ከባድ እና በወጣቱ ትውልድ ላይ ሸክም ሆነው ያሉ ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች የድነት ጥያቄዎች፣ የማንነት ጥያቄዎች፣ የወንጌል ጥያቄዎች ናቸው።

ዲጂታል ሚዲያ ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ከአቻቸው ተቀባይነትን ለማግኘት ግፊት ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ሱስ የሚያስይዝ የሶሻል ሚድያ ስበት ይሰማናል። ስማርት ስልኮቻችን ቢያንስ በ12 አቅጣጫ ተጽእኖ ያሳድሩብናል። ይሁን እንጂ እዚህ ጋር ጥያቄው ግልጽ ነው፦ እነዚህን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ይዘን ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ የሚገኙ ልጆች የባህሉን ጫና በመቋቋም፣ አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያለ ስማርት ስልኮች መኖር ይችላሉ ወይ? የሚል ነው።

ከስማርት ስልክ ነፃ የሆኑ ታዳጊዎች

“ይህ ሁሉን ይለውጣል፦ ወንጌል የልጅነት ወራትን ሲለውጥ” የተሰኘውን ድንቅ መጽሐፍ ለጻፈችው ዣክዌል ክሮው ከላይ የጠቀስኩትን ጥያቄ አንሥቼላት ነበር። እስከ 18 ዓመቷ ድረስ ስማርት ስልክ ያልተጠቀመች የ iGen ትውልድ ልጅ ምሳሌ ነች። ያንን ሁሉ ጊዜ መጠበቅ ምን ይመስል ነበር ብዬ ጠይቄያት ነበር፦

ዣክዌል ከልምድሽ ልታካፍዪን ጊዜ ስለሰጠሽኝ አመሰግናለሁ። ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ዘንድ ባሉ ልጆች የሚታየው ድባቴ እየጨመረ እንዳለ አንዳንድ ጥናቶች መጠቆም ጀምረዋል። ምንም እንኳ አንድ ብቸኛ ምክንያት ባይኖረውም በiGen ትውልድ ዘንድ የሚታየው የስማርት ስልክ መበራከት ግን እንደ ዋነኛ ምክንያት ይቆጠራል። እንዲህ ያለው በመካከላቸው የሚታየው ግንኙነት ያስደንቅሻል?

“በፍጹም። ስማርት ስልኮች፣ እየኖርንበት ላለው ዘወትር ተቀባይነት የመፈለግ አባዜ በከፍተኛ ሁኔታ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይህ የሚካድ ነገር አይደለም። ይህን ነገር ወላጆች የሚረዱት ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ክልል በነበረበት ጊዜ ባህላቸው የተገደበው በትምህርት ቤት ዙሪያ ነበር። ጠዋት 3 ሰዓት ገብተው ከሰዓት 9 ሰዓት ሲለቀቁ ወደ ቤተሰብ ሕይወት ድብርት ያቀናሉ።

አሁን ግን በቀን 24 ሰዓት በሳምንት 7 ቀን ሶሻል ሚዲያ ክፍት ነው። ሊታለፍ የማይችል ውድድር እና ከአቻዎች ተቀባይነት የመፈለግ ጨዋታ አለ። ሽባ የሚያደርግ አድካሚ እና ሊካድ በማይችል ሁኔታ የሚያጨናንቅ ነው። ከላይኮቹ፣ ከሼሮቹ፣ ከመልእክቶቹ እና ከምስሎቹ ዘወር ማለት አትችሉም። ማብቂያ የሌለው የዝነኝነት ፉክክር ይመስላል። ደግሞም በሁለቱም በኩል ይሠራል። ስማርት ስልክ፣ ከፊት ለፊት ቁጭ ብላችሁ ይህንን የዝነኝነት ፉክክር እንድትመለከቱ ያመቻችላችኋል።”

ይህ ነገር ኀይለኛ የሆነ መስተጋብር ነው። በሁለቱም አቅጣጫ (አስተዋጽኦ በማድረግ ወይም ውጤቱን በመመልከት) ዝነኛ የመሆን ባህልን አምልጦ መውጣት ከባድ ያደርገዋል። 18 ዓመት እስኪሆንሽ ስማርት ስልክ አልነበረሽም። ነገር ግን ስማርት ስልክ የነበራቸው ጓደኞች ነበሩሽ አይደል?

“አዎን ነበሩኝ። እንዲሁም በእኔ ዕድሜ የሚገኙት አብዛኛዎቹ እኔ የሌለኝ ነገር እንደ ነበራቸው በሚገባ አውቅ ነበር። ስልክ የነበራቸውን ጓደኞቼን ሁሉ መዘርዘር እችላለሁ። ምክንያቱም ስልካቸውን አይ ስለነበር ነው። አሊሰን ስልክ መያዝ ከጀመረች እሰማለሁ። ጄሬድም ስልክ መያዝ ከጀመረ እሰማለሁ። ስለሚጎርሩብኝ ወይም ስለሚያሸማቅቁኝ ሳይሆን ሁል ጊዜ በዙሪያዬ ስለነበር ነው። እያወራን እንኳ  ቢሆን ወይ ይጮሀል ወይ በእጃቸው ይዘውት ያገለባብጡታል። በመሀል ዝም ከተባባልን ወይም ጸጥታ ከሆነ ስልካቸውን ይመለከታሉ። እኔም በማይመች ጸጥታ እና መሰላቸት ውስጥ እንድቀመጥ ያደርገኛል።

በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ምን እየተካሄደ ነው ለሚለው ፍርሃቴ በሚገባ ምክንያት ሆኗል። በራስ መተማመን ማጣቴንም አጠንክሮታል። ምንም እንኳ ስማርት ስልክ ስላልነበረኝ ጓደኞቼ ደስ የማይል ስሜት እንዲሰማኝ ያደረጉኝ ባይሆንም፣ እንዲኖረኝ ግን ይጠብቁ ነበር። ስለዚህ እንዳልነበረኝ ሲረዱ ይገረማሉ። እኔ ከሌላው የተለየሁባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይህም ደግሞ ከጓደኞቼ መካከል ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልዴም መካከል ጭምር ነበር። በሞሎች ውስጥ ስዘዋወር ወይም ሰልፍ ስጠብቅ አሊያም በእግረኛ መንገድ ዳር ቆም ብዬ ዙሪያዬን እመለከታለሁ። ሙሉ ለሙሉ  በአካል ብገኝም ነገር ግን ከዚህ ዐውድ ተገንጥዬ  ስማርት ስልካቸው ላይ የተጣበቁ የታዳጊዎችን መዓት እመለከታለሁ። ብቸኛዋ እኔ እሆንና ምቾት የማይሰጥ ስሜት ይሰማኛል።

አንዳንድ ጊዜ ምንም እንኳ በሰዎች የተከበብኩ ቢሆንም ብቸኝነት ይሰማኛል። እነርሱ ሁልጊዜ በግንኙነት ውስጥ ያሉ እኔ ደግሞ የተገለልሁ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ይህንን ነገር ማግኘት ባለመቻሌ የተገደብኩ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሐሳቦች ስሜታዊ እና ጥልቅ ያልሆኑ መረዳቶች ከመሆን የዘለሉ አልነበሩም። ምክንያቱም በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በጊዜው ስልክ እንደማያስፈልገኝ ከቤተሰቦቼ ጋር ተስማምቼ ነበር።”

ወላጆችሽን ስለ አርቆ አሳቢነታቸው እና እምነታቸው በጣም አደንቃቸዋለሁ። በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ወላጆች ልክ ልጆቻቸው ለአቻ ግፊት እንደሚንበረከኩት፣ እነርሱም ከልጆቻቸው ለሚደርስባቸው ግፊት እጅ ይሰጣሉ። እኔም እንደ ወላጅ የሚሰማኝ ግፊት ነው። ይሁን እንጂ ይህን ውሳኔ በጥልቀት መመርመር ተገቢ ነው። ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ የሚሠራ ስማርት ስልክ ለልጆች መስጠት በቀላሉ ልንመልሰው የማንችለው ውሳኔ ስለሆነ ነው። ዕድሜዋ በዐሥራዎቹ ውስጥ እንዳለች ሴት፣ ዕድሜዬ 18 እስኪሆን መጠበቅ አለብኝ ብሎ ለመታመን ምን ያህል አስቸግሮሽ ነበር? ሁኔታው ከአቻዎችሽ ይልቅ ወላጆችሽን ይበልጥ መታመን ያለብሽ አንቺ እንደሆንሽ የሚገልጥ ይመስላል። ይህ ደግሞ የዚህ ዕድሜ ክልል ዋነኛ ትግል ነው።

“እርግጥ ነው መታመንን ይፈልጋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ለመገዛት እና ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። ወላጆቻችሁ ከምንም ነገር በላይ ለስሜታችሁ፣ ለአእምሯችሁ ጤንነት፣ ለመንፈሳችሁ፣ እንዲሁም ለአካላችሁ የተሻለ ነው ብለው የሚቆጥሩትን እንደሚያስቡላችሁ፣ እንዲሁም አቻዎቻችሁ ከሚያውቋችሁ በላይ እንደሚያውቋችሁ መረዳትን ይጠይቃል። “

ጉዳዩ በጣም ጥልቅ ነው፤ በርግጥ ብዙ ልጆች በውስጣቸው ይህንን ያውቃሉ። ነገር ግን ገፍተው የሚወጡት ስማርት ስልክ አለመያዝ ስለሚያሳፍራቸው ነው።

ስልክ ግን ሲያስፈልግሽ ማግኘት እንደምትችዪ እገምታለሁ?

“አዎ። ከቤት የምወጣ ከሆነ ለድንገተኛ ጉዳዮች የእናቴን ተከፋች ስልክ እዋሳለሁ። ይሁን እንጂ ተጠቅሜው አላውቅም ማለት ይቻላል።”

ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ነው። ዲጂታል ሚዲያን በተመለከተ ስማርት ስልክ ሳይኖርሽ በፊት ምን ትጠቀሚ ነበር?

“ኮምፒዩተር ነበረኝ። ኢሜል ነበረኝ። የተወሰኑ ሶሻል ሚዲያዎችንም መጠቀም እችል ነበር። በመሠረቱ ሁሉንም ነገር ከቤት ሆኜ ማድረግ እችላለሁ። ይሁን እንጂ ዘወትር እየተለጠጠ በመጣው የዲጂታል ዓለም ውስጥ እርሱም ቢሆን  የሆነ ያኽል የተገደበ ይመስላል።”

ልክ ነው። ልጆቻቸው በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሆኑ ወላጆች የሰጧቸውን ምስክርነቶች እያነበቡና ጥቅሙን እና ጉዳቱን በማመዛዘን ላይ ላሉ እንዲሁም በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ስማርት ስልክ ከመስጠት መዘግየት የተሻለ ነው ወደሚል ድምዳሜ እየደረሱ ላሉ ወላጆች፣ አሁን ላይ ሃያ ዓመቷ እንደሆናት ሴት ምን ትያቸዋለሽ። ከልጆቻቸው ምን ዐይነት ምላሽ መጠበቅ ይኖርባቸዋል?

“ለወላጆች ልጆቻችሁን መጠበቃቸሁ ትልቅ ዋጋ አለው እላቸዋለሁ። አይቼዋለሁ፤ ሰምቼአለሁ፤ ደግሞም የራሴን ስማርት ስልክ አሁን ስለያዝኩ ልመሰክር እችላለሁ ስማርት ስልክ ይለውጣችኋል።

የሚያስደንቁ እና የሚያስደነግጡ የግንኙነት በሮችን ይከፍትላችኋል። ትኩረት የማድረግ አቅማችሁን ያዳክማሉ። ከመጠን በላይ ሱስ የሚያስይዙ ነገሮች ናቸው። አጥር ልታበጁ ትችላላችሁ (ደግሞም ይገባችኋል፤) ግን ስማርት ስልክ በመሠረቱ ልባችሁን እና አእምሯችሁን ይለውጠዋል። ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ውስጥ ለሚገኙት ልጆቻችሁ፣ ይህንን ለውጥ ማዘግየት ምትችሉ ከሆነ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ይሆናል።

ስማርት ስልክ ከሚያመጣው አደጋ ጋር እንዲጋፈጡ አሳልፋችሁ ከመስጠታችሁ በፊት፣ ልጆቻችሁን ራስን መግዛት እና ማስተዋል እንዲኖራቸው አስተምሯቸው። እርግጥ ነው ስማርት ስልኮች በራሳቸው ክፋት የለባቸውም፤ ደግሞም ለመልካም ነገር መዋል ይችላሉ። ነገር ግን በጥንቃቄ ልንጠቀምባቸው ይገባል።

ልጆቻችሁን ስማርት ስልክ እንዲይዙ እስከ 18 ዓመታቸው የምታስጠብቋቸው ከሆነ፣ የሚሰማቸውን የሚያም የመገለል ስሜት አታጣጥሉ። ይልቁንም ይህንን ጊዜ ቴክኖሎጂን በጥበብ እና በታማኝነት እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የምታዘጋጁበት ይሁን። ባልተዘጋጁ እና ባልበሰሉ ልጆች እጅ የገቡ ስማርት ስልኮች የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ ነው።

ወላጆች ሊሰሟቸው ከሚችሉት ምላሾች ውስጥ ልጆቻቸው የተገለሉ እንደሆኑ እንደሚሰማቸው ነው። መረበሽ፣ ግራ መጋባት፣ ብቸኝነት ወይም መጎዳት እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ቁጣቸውንም ቢገልጡ በዚህ ምክንያት ነው። ከጓደኞቻቸው እንደ ተነጠሉ ሊሰማቸው ይችላል። የአቻ ግፊት ሕመም ሊሰማቸው ይችላል። የሚያመልጣቸው ነገር እንደሚኖር ሥጋት ይገባቸው ይሆናል። እንዲሁም በትክክልም የሚያሳስባቸው ነገር ሊኖር ይችላል (ለምሳሌ፦ ለብቻቸው ሲወጡ ስልክ መያዝ እንዳለባቸው ማሰብ)።

ወላጆች እንዲህ ያሉ ምላሾች ሲገጥሟችሁ ምክንያታችሁን ለማስረዳት ፍቃደኛ ሁኑ። ልጆቻችሁ ስማርት ስልክ መያዝ ለምን እንደማይፈቀድላቸው ሲጠይቋችሁ፣ “አትይዙም ስላልኩ” ዐይነት መልስ እንድትመልሱላቸው አይፈልጉም። ምንም እንኳ ከሐሳባችሁ ጋር ባይስማሙም፣ ምክንያታችሁን ለማስረዳት ፍላጎት ማሳየታችሁን እና በጉዳዩ ዙሪያ በጥልቀት ማሰባችሁን ግን አክብሮት ይሰጡታል።

በጉዳዩ ዙሪያ የሠራችሁትን ጥናት አጋሯቸው። ስማርት ስልክ ከሌላቸው ሌሎች ልጆች ጋር (በአካልም ይሁን ኢንተርኔት ላይ) አስተዋውቋቸው። እንደ ሕፃን ልጅ ከመቁጠር ይልቅ (“አይቻልም” ብቻ ብሎ ከማለፍ) ጥልቅ እና ከልብ የሆነ ውይይት ማድረግን ምረጡ። ውይይቱ እንዲቀጥል ፍቀዱላቸው። ስለሚሻለው የግንኙነታችሁ የላቀ ጥቅም ሲባል ከባዱን የውይይት ሥራ እናንተው ለመከወን ፍላጎት ይኑራችሁ።”

በጣም ጥሩ። በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙት ልጆች ልትያቸው በምትችይው ነገር መዝጋት እንችላለን። ከውስጣቸው እንዲሁም ከአቻዎቻቸው ምን ዐይነት ትግል ሊገጥማቸው እንደሚችል መጠበቅ አለባቸው?

“ይህንን ባህል የሚቃረነውን ርምጃ የምትወስዱ ልጆች ከትውልዳችሁ ወጣ ያላችሁ ናችሁ። በሕይወታችን ስንታዘዝ በክርስትና ሕይወታችን ሽክም የሚሆንብንን እና ተብትቦ የሚይዘንን ነገር ሁሉ ማስወገድ ይጠይቃል (ዕብራውያን 12፥1)። ላበረታታችሁ የምችለው ጸንታችሁ እንድትቆሙ ነው። ዋናው ነገር ይህ ነው። ጸንታችሁ ቁሙ።

ኢየሱስ ከስማርት ስልክ ይልቅ የተሻለ ነው። ይህንን እውነት በልባችሁ ደግሞ ደጋግሞ ታሰላስሉታላችሁ።

በመለየት እና በመነጠል ሸክም የከበደባችሁ ሲመስላችሁ አትጨነቁ። ማንነታችሁ በመመሳሰል ወይም ሥር ያልሰደዱ መስፈርቶችን በማሟላት ውስጥ ሳይሆን በክርስቶስ ውስጥ ብቻ ነው። እርሱም አንድ ኀላፊነት ይሰጣችኋል፦ ታማኞች እንድትሆኑ። አሁን ላይ ይህ ማለት ወላጆቻችሁን መታዘዝ እና ለእናንተ ያላቸውን መልካም አሳብ መታዘዝ ይሆናል። ይህም ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ስማርት ስልክ አለመያዝ ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከዚህ እውነታ አፍራችሁ አትሽሹ። ይልቁንም በእምነት ተቀበሉት። ደስታችሁ የሚገኘው በባህል ውስጥ ባለ ግንኙነት ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር በሚሆን አንድነት ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ! እንዲሁም ታማኞች ሁኑ። ሽልማታችሁ በመንገድ ላይ ነው። በዚህ ሕይወት አጣሁት ብላችሁ ከምታስቡት ነገር በላይ እጅግ የላቀ ነው።”